ኢሳት (ግንቦት 7 ፥ 2009)
መንግስት ለቀጣዩ አመት በሃገሪቱ ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ 180ሺ የእጅ ኮምፒውተሮች (ታብሌቶች) እንዲገቡ ያካሄደው የግዢ ጨረታ ውዝግብ ማስነሳቱ ተገለጸ።
የመንግስት ግዢዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሌኖቮ የተሰኘውን የቻይና ኩባንያ በተለያዩ መንገዶች በመገምገም ለጨረታው ተሳታፊ እንዳይሆን ቢወሰንም የኤጀንሲው የቅሬታ ሰሚ ቦርድ ግን ውሳኒው እንዲቀለበስ ማድረጉ ይታወሳል።
አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል የተባለው የኮምፒውተሮች ግዢ ከሌሎች አምስት ኩባንያዎች በኩልም የግልፅነት ተቃውሞ እየቀረበበት እንደሚገኝ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የቻይናው ኩባንያ በቦርድ በተሰጠው ልዩ ድጋፍ ለጨረታው እንዲያልፍ የተደረገበትን አካሄድ በመቃወም ቴክኖና ሪቮርስ የተሰኙ ኩባንያዎች ያቀረቡት አቤቱታ በተመሳሳይ መልኩ ውድቅ መደረጉም ታውቋል።
የቻይናው ሁዋዌና ሌኖቮ የተባሉት ድርጅቶች ወደ ፋይናንስ ግምገማ እንዲያልፉ የተደረገበት አካሄድ በአለም አቀፍ ኩባንያ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየቀረበበት እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
ተደጋጋሚ ቅሬታ እየቀረበበት ያለውን ይህንኑ ጉዳይ የመንግስት ግዢዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ እየተመለከተው እንደሆነ ምላሽን ሰጥቷል።
አጨቃጫቂ ሆኖ የቀጠለው የጨረታው የቴክኒክ ግምገማ ከመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከመረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በተውጣጡ ባለሙያዎች መካሄዱን ለመረዳት ተችሏል።
ዘመናዊ ኮምፒውተሮችን በግንቦት 2009 አም ግዢያቸው ተጠናቆ ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በተፈጠረው የጨረታ መዘግየት አቅርቦቱ ለአንድ ወር እንዲራዘም ተደርጓል።
በቀጣዩ አመት በሃገሪቱ ለሚካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ወደ ሶስት ቢሊዮን ብር አካባቢ በጀት የተመደበ ሲሆን፣ ኮምፒውተሮቹ አንድ ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጪ ይደረግባቸዋል ተብሏል።
ለቆጠራው 150ሺ ባለሙያዎች ይሰማራሉ የተባለ ሲሆን፣ የኮምፒውተሮቹ ቁጥር ከባለሙያዎች ቁጥር መብለጡ ጥያቄን አስነስቶ እንደነበር በወቅቱ መዘገባችን አይዘነጋም። የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ኮምፒውተሮቹ ለቆጠራ አገልግሎት ከዋሉ በኋላ ለተለያዩ መንግስታዊ የምርመር ስራዎች ይውላሉ ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
የአለም ባንክን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የፋይናስ ተቋማት ያለግልፅ ጨረታ በመንግስት የሚከናወኑ የዕቃ ግዢዎች ለሙስና የተጋለጡ ናቸው ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የአለም ባንክን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ያለግልፅ ጨረታ በመንግስት የሚከናወኑ የዕቃ ግዢዎች ለሙስና የተጋለጡ ናቸው ሲሉ በተደጋጋሚ ቅሬታን ሲቀርቡ ቆይተዋል።