ግንቦት ፯ ( አባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚደረገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየጨመረ ሲሆን፣ ዛሬም ከ40 በላይ ወታደሮችን የጫኑ ኦራል ተሽከርካሪዎች በወልድያ አድርገው ወደ ጎንደር አቅጣጫ አምርተዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርከሪዎች ወታደሮችን ወደ ሰሜን ሲያጓጉዙ ሰንብተዋል። በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው አዳዲስ ታንኮች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አዳዲስ ራዳሮችም በአፋር እና በሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች ተተክለዋል። ወታደራዊ እንቅስቃሴው እስካሁን ከነበሩት እንቅስቃሴዎች በስፋቱ የሚበልጥ ሲሆን፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ውጥረት ሊያባብሰው ይችላል።
የኢህአዴግ አገዛዝ ዋነኛ ጠላት ተድርጋ የምትታየው ኤርትራ፣ በኢትዮጵያ በኩል የሚታየውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አስምልክታ ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠችም። በኤርትራ በኩልም ምንም አይነት የተለየ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደማይታይ ምንጮች ይገልጻሉ።
በቅርቡ የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ጋር በማበር በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የሁለቱም መንግስታት ጠላቶች በተባሉ ሃይሎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቅኝት በማድረግ ላይ ናቸው። እስካሁን ድረስ ይህ ነው የተባለ የተጨበጠ ውጤት አለመገኘቱንም የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።