ኢሳት ( ግንቦት 4 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ በቱርኩ ጉለን ንቅናቄ ተቋቁመዋል የተባሉ ስድስት ትምህርት ቤቶች ማሪፍ ፋውንዴሽን ለተሰኘ የሃገሪቱ መንግስታዊ ተቋም ተላልፈው ተሰጡ።
ትምህርት ቤቶቹን የመረከብ ሂደት ከወራት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርት ቤቶቹን አስተላልፎ ለመስጠት የወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ የተካሄደ መሆኑ የፋውንዴሽኑ ተወካይ አደም ኮክ ለቱርኩ ዜና አገልግሎት (አናዱሉ) ገልጸዋል።
ባለፈው አመት በቱርክ የተካሄደውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ የቱርክ ባለስልጣናት የጉለን ንቅናቄ እጁ አለበት በማለት ተቋሙን በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ይታወሳል።
ቱርክ በንቅናቄው ላይ የወሰደችውን ይህንኑ እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ ሃገራት በድርጅቱ የተቋሙ ትምህርት ቤቶች ተላልፈው እንዲሰጧት ዲፕሎማሲያዊ ማግባባትን ስታደርግ ቆይታለች።
በቅርቡ በቱርክ ጉብኝትን ያደረጉ ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶቹን ሙሉ ለሙሉ አስተላልፋ እንደምትሰጥ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ በቱርክ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ነው የተባለው ማሪፍ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የሚገኙ ስድስት ትምህርት ቤቶችን ለማስተዳደር ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርት ቤቶቹን ለቱርክ አስተላልፎ እንደሚሰጥ ቃል ቢገባም በአዲስ አበባ የሚገኙ የትምህርት ቤቶች ተወካዮች ስድስቱ ትምህርት ቤቶች ለአንድ የጀርመን ባለሃብት መሸጣቸው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ይሁንና ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ትምህርት ቤቶቹ ተሸጠዋል በተባለው ጉዳይ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ የለም። የትምህርት ቤቶቹ ሃላፊዎች ተቋማቱን ገዝቷል ስለተባለው ማንነትና የገንዘብ መጠን ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአዲስ አበባ፣ አለም ገና እና መቀሌ የሚገኙት ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ በተከፈቱ ጊዜ በሃገሪቱ የሚገኙ የቱርክ የዲፕሎማቲክ ተወካዮች በክብር እንግድነት ተገኝተው እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና የቱርክ መንግስት የጉለን ንቅናቄ ከመፈንቅለ ሙከራው ጀርባ እጅ አለበት ማለቱን ተከትሎ ንቅናቄው በሽብርተኝነት ተፈርጆ ይገኛል።
የመንፍቅለ መንግስት ሙከራ መካሄዱን ተከትሎ የተቋቋመው ማሪፍ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የሚገኙትን ትምህርት ቤቶች በመረከቡ ደስታ እንደተሰማውና በኢትዮጵያም እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የቱርክ መንግስት በሌሎች ሃገራት የሚገኙ ተመሳሳይ ትምህርት ቤቶችን ለመረከብ ዲፕሎማሲያዊ ማግባባት እያደረገ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።
የጉለን ንቅናቄ ሃይማኖታዊ/መንፈሳዊ መሪ ፋቱላህ ጉለን እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1999 ጀምሮ በአሜሪካ በስደት ላይ ይገኛሉ፣ የቱርክ መንግስት ግለሰቡ ተላልፎ እንዲሰጠው ያቀረበው ጥያቄ ግን በአሜሪካ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ንቅናቄው በቱርክ ተሞክሯል ስለተባለው መፈንቀለ መንግስትም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ሲገልፅ ቆይቷል።