ግንቦት ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የአርበኛ ጎቤ የእህት ልጅ የሆነው ወጣት ዳዊት አንጋው ትናንትና ነው በወያኔ ታጣቂዎች ታፍኖ የተወሰደው።
ታጣቂዎቹ ወጣት ዳዊትን አፍነው የወሰዱበትም ምክንያት ያልተናገሩ ሲሆን፤ በጎንደር ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰረ ማረጋገጣቸውን ምንጮቹ ጠቅሰዋል።
አርበኛ ጎቤ መልኬ ያለፈውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ እጅግ በርካታ ሀብትና ንብረቱን ትቶ የሀገሩን ነጻነት ለማስከበር ከወያኔ ጋር ባደረገው እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ በርካቶችን ድባቅ የመታ፣ ለአገዛዙ ኃይላት ራስ ምታት የሆነና በመጨረሻም መደለያ በቀረበላት ዘመዱ አማካይነት የተሰዋ ስመ ጥሩ ጀግና መሆኑ ይታወቃል።
አገዛዙ በጎንደር፣በባህር ዳርና በተለያዩ ከተሞች ወደፊት አመጽ ይቀሰቅሱብኛል ብሎ የፈራቸውን ወጣቶች እያሳደደ መግደል፣ ማሰርና ማሰቃየትን ሥራዬ ብሎ እንደተያያዘው ከየከተሞቹ የሚደርሱት መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህም ባሻገር የወልቃይት ተወላጅ የሆኑ ወጣቶችን በአዲስ መልክ በጅምላ እያደኑ ማሰር መጀመራቸው ተመልክቷል።