ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2009)
የኬንያ የሳምቡራ ግዛት ሃላፌዎች ረቡዕ በኢትዮጵያ የጀመሩት የስራ ጉብኝት በግዛቲቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች ዘንድ የህዝብ ሃብትን ማባከን ነው በሚል ተቃውሞ ቀሰቀሰ።
በሰሜን ማዕከላዊ ኬንያ ስር የሚገኘው የግዛቲቱ የልዑካን ቡድን ዘጠን አባላት በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት የስምንት ቀን ቆይታ ከ58 ሺ ዶላር በላይ (ስድስት ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ) በጀት መያዛቸውን ዘ-ስታር የተሰኘ የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል።
ከተለያዩ የግዛቲቱ የስራ ሃላፊነት የተመረጡ የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የሁለት ቀን ስልጠና እንዲወስዱ ታውቋል።
የሳምቡራ ግዛት የልዑካን አባላት በምክር ቤት ይወስዱታል ከተባለው ስልጠና በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፓርላማና፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲሁም በአፍሪካ ህበርት ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል።
ይሁንና በቀን 4ሺ 500 ዶላር አካባቢ የቀን አበል እንዲከፈላቸው የተደረጉት የግዛቲቱ ተወካዮች ለጉብኝታቸው የመደቡት ከፍተኛ ገንዘብ ከተለያዩ አካላት ዘንድ መነጋገሪያ መሆኑ ታውቋል።
የግዛቲቱ ተወካይ የሆኑት ማራላል ሎልዴፒ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተደረገው ጉብኝት የህዝብ ገንዘብን ከማባከን ውጭ የሚያመጣው ጥቅም የለም ሲሉ ለዘስታር ጋዜጣ ገልጸዋል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ምክንያት በርካታ ህጻናት በምግብ እጥረት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ባለበት ወቅት ይህንን ያህል ገንዘብ ለጉብኝቱ መመደቡ አግባብ አይደለም በማለት ተወካዩ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ግብኝት እያደረጉ ያሉት የስራ ሃላፊዎች ወደኬንያ ሲመለሱ በመረጣቸው ህዝብ ዘንድ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያን እንዲሰጡ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በኬንያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ጉዳት እየደረሰባቸው ካሉ አካባቢዎች የሳምቡራ ግዛት አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ የተደረገው የስራ ጉብኝት ከቀናት በፊት ለግዛቲቱ የጸደቀን በጀት ተከትሎ እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል።
የቡድኑ አባላት በኢትዮጵያ እንደሚያደርጉት ጉዞ ለምግብ ዝግጅትና ተያያዥ የጉዞ ስራዎች 25 ሺ ዶላር አካባቢን በመመደብ አንድ አስጎብኚ ድርጅት መቅጠራቸውንም ዘ-ስታር ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
ይሁንና የግዛቲቱን በጀት ባጸደቁ ማግስት ወደ ኢትዮጵያ ያመሩት ዘጠኙ የልዑካን አባላት የህዝብ ገንዘብን ያለአግባብ አባክነዋል በሚል በኬንያ የፖለቲካና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተቃውሞ እየቀረበባቸው መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በጉብኝት ላይ የሚገኙት ሃላፊዎች እየቀረበባቸው ስላለው ተቃውሞ የሰጡት ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ የጉብኝቱ ጉዳይ ይመለከታቸዋል የተባሉ የግዛቲቱ አፈጉባዔ ስቴቭ ለሌግዌ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን ጋዜጣው አስነብቧል።