ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2009)
ለአለም ጤና ድርጅት ቀጣዩ ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ከመጨረሻዎቹ ሶስቱ ተፎካካሪዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከበርካታ ኢትዮጵያ ዘንድ እየቀረበባቸው ያለው ተቃውሞ ተጠናክሮ መቀጠሉን ግሎባል ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ የተሰኘ ጋዜጣ ዘገበ።
የአለም ጤና ድርጅቱ አባል ሃገራት በቅርቡ ቀጣዩን የድርጅቱ ሃላፊ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበራዊ ድረ-ገጾችን በመጠቀም የተቃውሞ ቅስቀሳን እያካሄዱ እንደሚገኝ ጋዜጣው አስነብቧል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳይመረጡ ዘመቻን እያካሄዱ ያሉት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ተፎካካሪው በሰብዓዊ መብት ጥሰትና በአፈናው የቆየ ታሪክ ያለው የገዢው የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ተዋንያን መሆናቸውን እየገለጸ መሆኑን ግሎባል ኢንፎርሜሽን ኔትዎርክ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰጥ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ ሪፖርትና በተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጭምር ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ይኸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በማሳሰብ ተቃውሞን እያሰሙ ያሉ ኢትዮጵያውያን የአለም ጤና ድርጅት ተቃውሞአቸውን እንዲሰማ እያደረጉ እንደሚገኝ ጋዜጣው አብራርቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያን የአለም ጤና ድርጅት ዋና ሃላፊውን ለመምረጥ በሚያደርገው ልዩ ጉባዔ ወቅት በዋና መቀመጫው ስዊዘርላንድ ጄኔቫ ከተማ የተቃውሞን ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሄዱ የሰልፉ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
የአለም ጤና ድርጅት አባል ሃገራት ከግንቦት 15 ፥ 2009 አም ጀምሮ ለአንድ ሳመንት በሚካሄደው አመታዊ ጉባዔ ቀጣዩን የድርጅቱ ሃላፊ ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁንና በዕለቱ ተቃውሞን ለማሰማት በዝግጅቱ ያሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች ዶ/ር ቴዎድሮስ በገዢው የኢህአዴግ መንግስት ውስጥ ያላቸው የቆየ አስተዋፅዖ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው በመሆኑ፣ የአለም የጤና ድርጅት ጉዳዩን እንዲረዳ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።
ከዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር የብሪታኒያና የፓኪስታን ተወካዮች ለመጨረሻ እጩነት ቀርበው የሚገኙ ሲሆን፣ የጤና ድርጅቱ አባል ሃገራት በሚስጥር በሚሰጡት ድምፅ ቀጣዩን ዋና ዳይሬክተር ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።