የኢትዮጵያ ብርድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ በሙስናና በብልሹ አሠራር ተተብትቧል በተባለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

ግንቦት ፫ ( ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርላማው ሪፖርታቸውን ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኮንን እና የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑትየመንግሥት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤በሥራቸው ጣልቃ የሚገቡ ባለስልጣናት ኮርፖሬሽኑ ተቋማዊ ነጻነቱ ጠብቆ እናዳይጓዝ እንቅፋት እንደፈጠሩባቸው መናገራቸው ይታወሳል።ሪፖርት አቅራቢዎቹ በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ቡድንተኝነት፣ ዘረኝነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር መኖሩን በይፋ ማመናቸውን ተከትሎ የሚመለከተው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮምቴ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ ባዘዘው መሠረት፤ በዛሬው እለት የፓርላማው የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴየውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል፡፡ኮርፖሬሽኑ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ሕዝቡን ያሳተፈ የሚዲያ ሥራ ለማከናወን አለመቻሉን፣ የአሠራር፣ የክህሎትና የአመለካከት ችግሮች በተቋሙ ውስጥመንሰራፋታቸውን ያስቀመጠው ቋሚ ኮሚቴው ፤ ኮርፖሬሽኑ የኤዲቶሪያል ነጻነት እንዳለው በፖሊሲው የተደነገገ ቢሆንም፤ በውስጥና በውጪ አካላት ጣልቃገብነትና ተጽዕኖ በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻሉን ጠቁሟል።ኮሚቴው አክሎም፦” ጠባብነት፣ ቡድንተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና በቤተሰብ መሳሳብ በተግባርና በአመለካከት በኮርፖሬሽኑ ይታያል” ብሏል።ኮርፖሬሽኑ ችግሮቹን በተሟላ ሁኔታ ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሃሳብ የያዘ ሪፖርት በ15 ቀናት ጊዜያት ውስጥ ለፓርላማው እንዲያቀርብያዘዘው ቋሚ ኮሚቴው፤ ጣልቃ ይገባሉ የተባሉ በስም ያልተገለጹ አካላት እጃቸውን እንዲሰበስቡ ሲል አስጠንቅቋል፡፡ተቋሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መርህ እንዲመራ እና የሥራ አመራር ቦርዱም በጥናት ላይ የተመሠረተ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችላል በማለት ቋሚ ኮሚቴው ያስቀመጠው የውሳኔ ሃሳብ በፓርላማው ጸድቋል፡ሆኖም ይህ የፓርላማው ውሳኔ – ከውሳኔነት አልፎ በአስፈጻሚው አካል ተቀባይነት ያገኛል ወይ? አስፈጻሚው አካል እንደተባለው እጁን ከሚዲያው ላይአንስቶ በነጻነት ሊለቀው ይችላል ወይ? የሚለው አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ነው።ቀደም ብሎ አቶ በረከት ስምኦን በቦርድ ሰብሳቢነት ይመሩት የነበረውን ይህንኑ ተቋም «ያልተጠረገ በረት» ሲሉ መዝለፋቸው የሚታወስ ነው።