የአዲስ አበባ ነጋዴዎችን በግብር ስም መዝረፉ ተባብሶ ቀጥሏል

ግንቦት ፫ ( ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ ንግድና የገቢዎች ቢሮ በተጨማሪ የዋጋ ግብር ማለትም በቫት አዋጅ ስም የድርጅቱን ሠራተኞች ገንዘብ እየሰጠ በሰላይነት በማሰማራትነጋዴዎች ላይ ምዝበራ እየፈጸመ መሆኑን ነጋዴዎች አጋለጡ።
ነጋዴዎቹ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የአገዛዙ ሹመኞች ነጋዴዎችን ከሕግ አግባብ ውጪ በመክሰስና የሃሰት ምስክሮችን በማቆም የነጋዴው ማህበረሰብንማሰርና ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መቀጮ ማስስከፈል ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል።
የንግድና ገቢዎች ቢሮ በሚልካቸው ሰላዮች አማካኝነት ምዝበራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚገልጹት ነጋዴዎቹ፤ የቢሮዎቹ ሰላዮች በየሳምንቱ ወደሥራቦታቸው እየመጡ ከአምስት ሺህ ብር በላይ ጉቦ እየተቀበሉዋቸው መሆኑን በምሬት ተናግረዋል።
የቢሮዎቹ ሰላዮች፤የተጠየቁትን ጉቦ የመክፈል አቅሙ የሌላቸውን ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶች እስከ ማዘጋት መድረሳቸውም ተመልክቷል።
ከዚህም በላይ ንግድና ገቢዎች ቢሮ ከሰሞኑ በንግድ ቤቶች ላይ የቁርጥ የቀን ገቢ ግምት ማውጣት የሚል ዘመቻ መጀመሩን የገለጹት ነጋዴዎች፤ ገማቾቹ፤ንግድ ቤቶቹ በሳምንትም የማያስገቡትን ገቢ በቀን ሽያጭ እየገመቱ ድርጅታቸውን እንዲዘጉ እያስገደዷቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ግምቱ እንዲቀንስላቸውና ድርጅቶቻቸው ከመዘጋት እንዲተርፉ ከፈለጉ፤ ለሶስትና አራት ገማቾች የዓመት ትርፋቸውን የሚያክል ጉቦ በጉዳይ አስፈጻሚደላሎቻቸው በኩል እንደሚጠየቁ ነጋዴዎቹ አጋልጠዋል።
ነጋዴዎች በመጨረሻም፦ ”በአንድ በኩል በቫት፣ በሌላ በኩል በቀን ሺያጭ ግምት እንዲህ የሚያሰቃዩን ተማረን የንግድ ፈቃዳችንን እንድናስረክብ በማሰብነው። ፈቃዳችንንና የንግድ ቤቱን እንድናስረክብ የተፈለገውም፤ ለገዥው ፓርቲ ሰዎች ለመስጠት ታስቦ ነው። ችግሩ ከአቅማችን በላይ እየሆነ ስለመጣ ያለን ብቸኛ አማራጭ ድርጅታችንን ዘግተን መሰደድ ብቻ ነው።” ሲሉ ብሶታቸውን በምሬት ገልጸዋል።