የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አበድሮ የማይሰበስበው የገንዘብ መጠን በሃላፊዎች መካከል አለመግባባት መፍጠሩ ተነገረ

ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለተለያዩ ተበዳሪዎች አበድሮ የማይሰበስበው የገንዘብ መጠን በሃላፊዎች መካከል አለመግባባት ፈጠረ።

ባለፈው ሳምንት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ አራት ምክትል ፕሬዚደንቶች በዚሁ ተመላሽ በማይሆን የብድር መጠን ከባንኩ ፕሬዚደንት ጋር ባለመስማማታቸው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ምክንያት መሆኑን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት አቶ ጌታሁን ናና የባንኩ የተበላሸ ብድር (nonperforming loans) መጠን ወደ 50 በመቶ አካባቢ ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ ማቅረባቸው ታውቋል። 

ይሁንና አራቱ ተሰናባች ፕሬዚደንቶች ባንኩ ለተለያዩ አካላት አበድሮ የማይሰበስበው የብድር መጠን ሃላፊው ከሚገልፁት ጋር እጅጉኑ የሚለያይ እንደሆነ በመግለጻቸው ከአዲሱ ፕሬዚደንት ጋር አለመግባባታቸው ታውቋል።

በአዲሱ የልማት ባንክ ፕሬዚደንትና በስራ ሃላፊዎቹ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ አቶ ጌታሁን ናና አራቱ ምክትል ፕሬዚደንቶች ከሃላፊነት እንዲነሱ ማድረጋቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለበርካታ ተበዳሪዎች ከሚሰጠው በቢሊዮን ብር ከሚቆጠር ብድር ውስጥ ከፍተኛ ገንዘቡን በተበላሸ ብድር ስም እንደማይሰበሰብ ተመልክቷል።

የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን እያሰፉ መምጣት ባንኩን አደጋ ውስጥ ከመክተቱ በተጨማሪ፣ ለፋይናንስ ቀውስ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የባንክ ባለሙያዎች በበኩላቸው አዲሱ የልማት ፕሬዚደንት ከ20 አመት በላይ በዘርፉ ልምድ ያላቸው ሃላፊዎች በቁጥር ልዩነት ማሰናበቱ ተገቢ አይደለም ሲል ለጋዜጣው አስረድተዋል። ይሁንና የልማት ባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ጌታሁን ከባልደርቦቻቸው የቀረበው መከራከሪያ አሳማኝ አለመሆኑን በሰጡት ምላሽ አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅትም የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ወደ 20 በመቶ አካባቢ የሚደርስ ነው ሲሉ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ባቀረበው የስድስት ወር ሪፖርቱ የባንክ የተበላሸ የብድር መጠን ከአለም አቀፍ ደረጃ በመበልጥ 16 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። ይሁንና ባንኩ ይፋዊ ነው ያለው አህዝ በባሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች ዘንድ መከፋፈል መፍጠሩን ለመረዳት ተችሏል።

ከምክትል ፕሬዚደንትነታቸው የተነሱት አራቱ ሃላፊዎች የወደፊት እጣ ፈንታቸው ያልታወቀ ሲሆን፣ በምትካቸው አቶ ሃይለየሱስ በቀለ አቶ ሃዱሽ ገብረእግዚያብሄር፣ አቶ ጌታቸው ዋቄ፣ እና አቶ እንዳልካቸው ምህረቱ የተባሉ ሃላፊዎች መሾማቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የሃላፊዎች ሹመት ለብሄራዊ ባንክ ቀርቦ በስድስት ወራቶች ውስጥ መጽደቅ እንዳለበትም ታውቋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ የእርሻ መሬት ከሰጠው ብድር ጋር በተያያዘ በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ኪሳራ እንደደረሰበት ይታወሳል።

ባንኩ በአሁኑ ወቅት 36 ሚሊዮን ብር አካባቢ ለብድር ሰጥቶ የሚገኝ ሲሆን፣ የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው አዲስ መመሪያ በንግድ ባንክ በኩል ለልማት ፕሮጄክቶች ሲሰጥ የቆየው ብድር ወደ ልማት እንዲዛወር ማደረጉም አይዘነጋም።