የማላዊ መንግስትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማላዊ አየር መንገድን በሽርክና ለማስተዳደር ያደረጉት ስምምነት ተቃውሞ ቀረበበት

ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2009)

በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማላዊ መንግስት ጋር የማላዊን አየር መንገድ በሽርክና ለማስተዳደር ያደረጉት ስምምነት በማላዊ የፓርላማ አባላት ዘንድ ተቃውሞ ቀረበበት።

በሃገሪቱ ፓርላማ ተሰሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፓርላማ አባሏ ጁሊያን ሉንጉዚ የሃገራቸው መንግስት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረገው ስምምነት ማላዊን የሚጠቅም አይደለም በማለት ውሉ መጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄ ማቅረባቸውን ኒያሳ ታይምስ የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል። 

የማላዊ ኮንግረስ ፓርቲ አባሏ ሉንጉዚ ለፓርላማ ባደርጉት ንግግር የተደረሰው ስምምነት ማላዊን ስለመጥቀሙ የማላዊ መንግስት ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

እርሳቸውን ጨምሮ የተለዩ የፓርላማ አባላት የተደረገው ውል ማላዊን የሚጠቅም እንዳልሆነ መረጃ እየደረሳቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ አነጋጋሪ ጉዳይ ዙሪያ የማላዊ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሃገሪቱ ጥቅም ታገኝበታለች በተባለው ውል ማብራሪያን እንዲሰጥ የፓርላማ አባሏ አክለው ማሳሰባቸውን ኒያሳ ታይምስ ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማላዊ መንግስት ጋር በቅርቡ በደረሰ ስምምነት መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ ድርሻን ለመያዝ የሚችል ሲሆን፣ የተቀረው 51 በመቶ ድርጃ ደግሞ የማላዊ መንግስት እንዲሆን ተወስኗል።

በሽርክና የሚተዳደርው የማላዊ አየር መንገድ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡና በደቡባዊ አፍሪካ የሚደረጉ በረራዎችን በተጠናከረ መልኩ ለመስራት እቅድ መንደፉ ታውቋል።

ይሁንና ስምምነቱ በማላዊ በፓርላማ አባላት ጥያቄ ማስነሳቱ አሉታዊ ተፅዕኖን ሊያሳድር ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆን፣ የማላዊ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ የሰጡት ምላሽ የለም።