ኢሳት (ግንቦት 1 ፥ 2009)
ከ90 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ በአለም ካሉ ሃገራት መካከል ያልተመጣጠነ የዜጎች ገቢን በማስመዝገብ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መፈረጇ ተገለጸ።
ሃገሪቱ ባለፉት 10 አመታት የባለ ሁለት አህዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን አስመዝግባለች ቢባልም፣ ኢትዮጵያ አሁንም ድረስ በድህነት ውስጥ ከሚገኙ ሃገራት ተርታ አንዷ መሆኗን ወርልድ ኢኮኖሚስ ጋዜጣ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል። በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን አማካኝ የነፍስ ወከፍ ገቢ 590 ዶላር ሲሆን፣ መጠኑም በአፍሪካ ሆነ በአለም ደረጃ ዝቅተኛው መሆኑ ተመልክቷል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት አማካኝ የዜጎቻቸው ገቢ ወደ 1ሺ ዶላር አካባቢ የደረሰ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተመዝግቧል የተባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ የተጠበቀወን ያህል ዕድገት (ጭማሪ) አለማሳየቱም ታውቋል።
ሺሸልስና ኢኳቶሪያል ጊኒ ከ15 እና ከ14 ሺ ዶላር በላይ የነፍስ ወከፍ ገቢን ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ኬንያ 1ሺ 522 ዶላር ገቢን ለማስገኘት በቅታለች። ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲና፣ ማላዊ ከአፍሪካ ከ300 ዶላር በታች የነፍስ ወከፍ ገቢን በማስመዝገብ የመጨረሻዎቹ ሶስቱ ሃገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ አሁንም ድረስ 24 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት በከፋ የድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ የዜጎች ገቢ እጅጉኑ ያልተመጣጠነ መሆኑን ወርልድ ኢኮኖሚክስ የተለያዩ አሃዞችን በማሳያነት በማቅረብ በሪፖርቱ አስፍሯል።
ባለፈው አመት በሃገሪቱ ተከስቶ የነበረው የድርቅ አደጋና ህዝባዊ አመፅ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ አስተዋጽዖ እንዳሳደረ ያወሳው ጋዜጣው፣ የኢትዮጵያ የባለፈው አመት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሃገሪቱ አጠቃላይ አመታዊ ምርት ጋር ሲነጻጻር 5.4 በመቶ ሆኖ መመዝገቡንም አለም አቀፉ ጋዜጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ በማድረግ አስነብቧል።