ግንቦት ፩ ( አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ ወያነ ኃርነት ትግራይ ዋና የሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት መመረጥ የለባቸውም ያሉ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ታላቅ አውሮፓ አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ።
እንደ ሰልፉ አስተባባሪዎች ገለጻ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት በሚደረገው በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከመላው አውሮፓ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከመላው አውሮፓ ወደ ስፍራው ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“የቴዎድሮስ አድሀኖም ቦታ ዘ ሄግ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት እንጂ የዓለም ጤን ድርጅት ቢሮ ሊሆን አይገባም “ የሚሉት አስተባባሪዎቹ፤ ዜጎቹ በቆሻሻ ክምር እስኪሞቱ ድረስ ምንም ያልሰራ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የዓለም ጤና ድርጅትን የሚመራበት ምንም ዓይነት የብቃትንም ሆነ የሞራል መሰረት አይኖረውም ብለዋል።
ህወኃት በዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለው ግድያና ግፍ የሚሰማቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የፊታችን ሜይ 22 በጄኔቫ የተመድ ጽህፈት ቤት በሚደረገው በዚህ ታላቅ ሰልፍ ላይ በመገኘት በህወኃቱን ቁንጮ አስፈጻሚ ብረቴዎድሮስ አድሀኖም ላይ የተቃውሞ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ አስተባባሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ከሚወዳዱት እጩዎች መካከል ዶክተር ቴዎድሮስን ጨምሮ ሦስት የቀሩ ሲሆን፤ቀሪዎቹ ሁለቱ እንግሊዛዊው የተመድ ሠራተኛ ዶክተር ዴቪድ ናባሮ እና ፓኪስታናዊዋ የጤና ባለሙያ ዶክተር ሳኒታ ኒሽታር ናቸው።