ግንቦት ፩ ( አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ሲንገላታ በቆየው በወጣት ሙጂብ አሚኖ ክስ ጉዳይ ዛሬ ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም ያስቻለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት፤ የመከላከያ ምስክሮች ላይብይን ለመስጠት የተሰጠውን የጊዜ ቀጠሮ አራዘመ።
ወጣት ሙጂቦ ፣በእነ ኤሊያስ ከድር የክስ መዝገብ በሃሰት አልመሰክርም በማለቱ፣ እንዲሁም በእነ ከድር መሃመድ የክስ መዝገብ የተከሠሱትን እነ አቡበከር አህመድን በኃይል ለማስፈታትሞክረሃል የሚሉ ሁለት የሃሰት ክሶች ቀርበውበታል።
በሁለት የክስ መዝገቦች የተከሰሰው ወጣት ነጂብ በአንዱ ክስ የአምስት ዓመት ከስድስት ወራት እስር ተፈርዶበታል።በሁለተኛው የክስ መዝገብ ላይ መከላከያ ምስክሮችን ለማሰማት ዛሬ ችሎት ላይ ቢቀርብም፤ ፍርድ ቤቱ ”የመከላከያ ምስክሮች የድምጽ ፋይል ስለጠፋ” በሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያትየመከላከያ ምስክሮቹን ለግንቦት 9 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲያቀርብ በማለት ዳግም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ወጣት ሙጂብ አሚኖ በዛሬው ችሎት እህቱን ቀድርያ አሚኖን እና ጠበቃ ተማም አባቡልጉን ጨምሮ ወጣት ሃሽም አብደላን፣ ኢልያስ ከድርን፣ ጃፈር ዲጋን፣ አብዱል አዚዝ ፈትሁዲን፣ ፋሩቅሰኢድን፣ ሃያተል ኩብራን፣ መሬማ ሃያቱን እና ሌሎች መከላከያ ምስክሮችን በአካል አቅርቦ ነበር።
ቀጠሮው መራዘሙን ተከትሎ፦”ምስክሮችህን ዳግም ማቅረብ ትችላለህ ወይ?” ተብሎ ከፍርድ ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄ ወጣት ሙጂብ ሲመልስ ”መጀመሪያም መከላከያ ምስክሮች አቅርቤየተከላከልኩት በታሪክ ላይ እንዲመዘገብልኝ ነው። አሁንም ቢሆን መከላከያዎች ከበቂ በላይ ስላሉኝ እከላከላለሁ” ብሏል።
ከሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ተከሳሾች ውስጥ በእድሜ ትንሹ ይኸው በዓላማው ጽኑ የሆነው ወጣት ሙጂብ አሚኖ መሆኑ ይታወቃል።