ኢሳት (ሚያዚያ 30 ፥ 2009)
የሱዳን መንግስት በቀይ ባህር ላይ በሚገኘው የሃይላብ ግዛት ላይ ያነሳውን የይገባኛል ጥያቄ ተከትሎ ግብፅ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቃውሞ አቀረበች።
ግብፅና ሱዳን በአዲስ መልኩ የገቡበት ይኸው የድንበር ይዞታ ውዝግቡ በአባይ ግድብ ላይ በመካሄድ ላይ ባለው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል። የሱዳን መንግስት በግዛቱ ላይ ያነሳውን የይገባኛ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል ያለውን አዲስ ሃሳብ ከወራት በፊት ማቅረቡ ይታወሳል።
ይሁንና የሃይላብ ግዛትን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥራ የምትገኘው ግብፅ በሱዳን በኩል የቀረበን ማንኛውንም የይገባኛል ጥያቄና የመፍትሄ ሃሳብ እንደማትቀበል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባቀረበችው አቤቱታ መገልጿን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።
ከቀናት በፊት ለድርጅቱ ተቃውሞን ያቀረበው የግብፅ መንግስት በሱዳን መንግስት ለሚነሱና ለሚደርሱ ማንኛውም የግዛቲቱ የባለቤትነት ጥያቄ እውቅናን እንደማይሰጥ አስታውቋል። ሱዳን ከብሪታኒያ አስተዳደር ስር እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1958 ነጻ ከወጣች በኋላ የግዛቲቱ ጥያቄ በሁለቱ ሃገራት መካከል አለመግባባት ፈጥሮ መቆየቱ ታውቋል።
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ይህንኑ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ይቀረፋል ያሉት ሃሳብ ጥናት እንዲካሄደበትና በአስቸኳይ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይሁንና አዲሱ ሃሳብ ተጠናቆ ሲያልቅ ግብፅ ከቀናት በፊት ድርጊቱን በመቃወም ለተባበሩቱ መንግስታት ድርጅት አቤቱታን ያቀረበች ሲሆን፣ የሃይላይብ ግዛትም በማንኛውም ሁኔታ ለድርድር እንደማይቀርብ ገልጻለች። ሁለቱ ሃገራት ዜጎቻቸው ያለመግቢያ ፈቃድ ቪዛ እንዲዘዋወሩ ስምምነት ቢኖራቸውም ግብፅ ከአንድ ወር በፊት ስምምነቱን ማፍረሷ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅት በሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ያነሳችበት የቀይ ባህር አካባቢ ግዛት በግብፅ ወታደራዊ ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን፣ ሱዳን ድርጊቱን በመቃወም ዕርምጃው ወታደራዊ ወረራ ነው ስትል ትገልጻለች።
የሱዳኑ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር በጉዳዩ ዙሪያ ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር ቀጥተኛ ንግግር እንዲካሄድ ጥያቄን ቢያቀርቡም ግብፅ የድንበሩን ስፍራ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም በማለት ጥያቄውን ሳትቀበል ቀርታለች። አለም አቀፉ አካል የሁለቱን ሃገራት ጉዳይ ለመመልከት በሁለቱ ወገኖች መካከል ፈቃደኝነት ማግኘት የሚኖርበት ከተማ ሲሆን ግብፅ ያቀረበችው ይኸው ተቃውሞ ጉዳዩ በሶስተኛ አካል እንዳይታይ እንደሚያደርገው ለመረዳት ተችሏል።
ሁለቱ ሃገራት የገቡበት ይኸው ውዝግብ ከኢትዮጵያውያን ጋር በአባይ ግድብ ዙርያ በመካሄድ ላይ ባለው ድርድር የራሱን ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።