ሚያዝያ ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- አምባሳደሩ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያዬት በሚል ነበር በመኖሪያ ቤታቸው የህወኃት- ኢህአዴግ አባላት የሆኑ ሰዎችን በምስጢር ስብሰባ የጠሩት።
ስለ ጥሪው የሰሙ በስዊዘርላንድ የሚገኙ ሀገር ውዳድ ኢትዮጵያውያን “የሀገራችን ጉዳይ እኛንም ያገባናል” በማለት በቀጥታ ስብሰባው ወደተጠራበት ወደ አምባሳደሩ ቤት ሰተት ብለው ይገባሉ።
ሁኔታው ስጋትና ጭንቀት ያሳደረባቸው የስብሰባው አስተባባሪዎች ልክ እንደ ጸጉረ ልውጥ የህወኃት አባላት ያልሆኑትን ኢትዮጵያውያን ከስፍራው ለማስወጣት ሲሞክሩ ከፍተኛ ረብሻና ተቃውሞ ሊነሳ ችሏል።
የኢትዮጵያውያኑ ተቃውሞ እያዬለ በመምጣቱ ከፍ ያለ ፍርሀት ውስጥ የወደቁት አምባሳደሩ ስልክ በመደወልና “ድረሱልን” በማለት ከ20 በላይ ፖሊሶችን በማስመጣት ተቃዋሚዎቹን ለማስወጣት ቢሞክሩም፤ ኢትዮጵያውያኑ “ በሀገራችን ጉዳይ በሚመክር ስብሰባ ላይ የመሳተፍ መብት ስላለን አንወጣም!” በሚል አቋማቸው በመጽናታቸው ስብሰባው ለሰዓታት ሊቋረጥ ችሏል።
በስተመጨረሻም የፖሊስ ኃላፊው ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ባደረጉት ውይይት መግባባት ላይ በመደረሱና “ቦታው የአምባሳደሩ መኖሪያ ቤት ስለሆነ ልቀቁላቸው” በመባሉ ኢትዮጵያውያኑ በፖሊሶች ታጅበው ከቦታው ለቀዋል።ተመርጠው ስብሰባውን ሊካፈሉ የሄዱት የህወኃት ተላላኪዎች ከ25 እንደማይበልጡ ኢትዮጵያውያኑ ገልጸዋል።
“ከሁሉ የሚገርመው ስብሰባው የተደረገበት በአምባሳደሩ መኖሪያ የሚገኘው ቦታ እጅግ አስፈሪና ወደ ውስጥ ብዙ ደረጃ የሚያስወርድ ጉድጓድ ውስጥ መሆኑ ነው”ያሉት ኢትዮጵያውያኑ፤“ይህ የሚያሳዬው የሽፍቶቹ ገዥዎች የፍርሃት መጠን ልኩን ማለፉን ነው” ሲሉ ለኢሳት አስተያዬታቸውን ገልጸዋል።