ሚያዝያ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተለያዩ ተቃውሞዎችን ስታስተናገድ በከረመችው ደንቢያ፣ የተጠራው ስብሰባ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እንደቀረበበትና ስብሰባው ተቋርጦ እንደነበር ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የወረዳው አስተዳደር ዘይት እናከፋፍላለን በማለት ህዝቡ በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ያደረገ ቢሆንም፣ የዘይት ችግር የሚለው አጀንዳ ተለውጦ ስለሰላም እና ስለጸጥታ ንግግር በሚደረግበት ወቅት፣ ህዝቡ “ ዘይት ብላችሁ ነው የጠራችሁን፣ አሁን የምታወሩን ሌላ ነገር ነው” በማለት ስብሰባውን ጥሎ ሲወጣ፣ የመድረክ መሪዎቹ “ ዘይትም አለ” በሚል ተሰብሰቢውን መልሰውታል።
አሁንም ስብሰባውን በተመሳሳይ ስብከት ለመጀመር ሙከራ ሲደረግ፣ ህዝቡ የመብት ጥያቄዎቻችን ይመለሱልን በማለት ጥያቄ አቅርቧል። 26 ዓመታት ጥያቄዎችን ጠይቀን መፍትሄ አልተሰጠንም፣ አሁንስ ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ምን መፍትሄ ታመጣለህ በማለት የተለያዩ ጥያቄዎችን የጠየቁ ሲሆን፣ የስብሰባው መሪ “ ይህ ከእኛ አቅም በላይ ነው” በማለት መልስ ሰጥቷል። ስብሰባው የተጨበጠ ነገር ሳያስገኝ ተበትኗል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ ፍንዳታዎችን በማስተናገድ ላይ ያለው የሰራቫ ፕሮጀክት ጠባቂ ወታደር በጥይት ተመትቶ በመቁሰሉ ፣ አቶ አደራጀው ጋሹ የተባሉ ግለሰብ ተይዘው ታስረዋል።