ሚያዝያ ፳፯ ( ሃያ ሰባት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዞኑ ደህንነት ሃላፊ አቶ አልአዛር ቶይሳ ፍላጎት ከ4 ወር በላይ የታሰሩት የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት/ ኦህዲኅ/ ም/ል ሊቀመንበር መምህር ዓለማዬሁ መኮንን በ3000 /ሦስት ሺህ) ብር ዋስ 07/07/2009 ዓ.ም. ከተፈቱ በሁዋላ፣ ያቀረቡት ክስ መቃወሚያ ተቀባይነት አግኝቶ ከወንጀሉ ነጻ ተብለዋል ፡፡
‹‹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ‹‹ የጥቁር መልበስ ድንበር ተሻግሮ ጥቁር ልብስ በሣጥን ማስቀመጥም ወንጀል ሆኖ አስር ወር ያስፈርዳል›› ያሉት የድርጅቱ ከፍተኛ የአመራር አባል፣ ‹‹ ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስሮ የነበረው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ኅብረት የዞኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ዳዊት ታመነ በግፍ የተገደለውን የሣሙኤል አወቀ ፎቶ ያለበት ጥቁር ቲሸርት ከሳጥኑ መገኘቱ ብቻ ወንጀል ሆኖበት የጂንካ ከተማ ፍርድ ቤት የአስር ወራት እስራት ፈርዶበት ወህኒ እንዲወረወር “ መደረጉን አስረድተዋል።
እነዚህ ተገኙ የተባሉት ቲሸርቶች ደግሞ የታተሙትና የተሰራጩት በአገሪቱ ህግ መሰረት ተመዝግቦ በእንቅስቃሴ ላይ በሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ቅጥር ግቢ በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በግልጽና በአደባባይ ሲሆን፣ ይህንን በሚመለከት ወጣት ዳዊት ይግባኝ ጠይቆ ውጤቱን በመከታተል ላይ እያለ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተመሰረተው ክስ ውድቅ ተደርጓል።
በአቶ ዓለማዬሁ ላይ የደረሰው ሥነልቡናዊ ጉዳት ፣ በቤተሰብ ላይ የደረሰው እንግልትና ማኅበራዊ ጫና ፣ ለማኅበረሰቡ የተላከው ‘ የእኔን ያየህ ተቀጣ’ ማስፈራሪያ የሚያስከትለው መሸማቀቅ ሳይረሳ፣ ያለወንጀል በጥርጣሬ አስሮ መፍታትን ዝም ብሎ መቀበል ‹‹ ያለጥፋት ፈርዶ ወደ ማሰር እየተሸጋገረ በመሆኑ ልምታገለው ይገባል ብለዋል። እነ አቶ አለማየሁ ከክሱ ነጻ በመባላቸው ግን ደስታቸውንም አልሸሸጉም።