ሰሜን ኮሪያ የአገሪቱን መሪ ኪም ጆን ኡንን በባዮ-ኬሚካል ንጥረ ነገር በመመረዝ ለመግደል የታቀደው ሴራ መክሸፉ ገለጸች

ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)

የግድያ ሴራውን አስመልክቶ የሰሜን ኮሪያ የመንግስት ዜና አገልግሎት ድርጅት እንደገለጸው፣ በሰሜን ኮሪያ በህቡዕ የሚሰራ አሸባሪ ሃይል ከአሜሪካው የስለላ ድርጅት (CIA)ና ከደቡብ ኮሪያ የጸጥታ አገልግሎት (IS) ጋር በመተባበር ጥቃቱን ለመፈጸም አቅደው እንደነበር ገልጿል።

የሰሜን ኮሪያ የዜና አገልግሎቱ በታላቁ መሪ ማለትም ኪም ጆን ኡንን ላይ ታቅዶ ስለነበረው የመግደል ሙከራ የሰጠው ምንም አይነት ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም፣ ሴራው በቅርብ ጊዜ ተደርሶበት በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ሲል አስታውቋል። የአሜሪካው የስለላ ድርጅት CIA እና፣ የደቡብ ኮሪያው የጸጥታ አገልግሎ IS ለአንድ የደቡብ ኮሪያ ዜጋ የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ በማድረግ አደጋውን ለማድረስ መንቀሳቀሳቸውን ይኸው የዜና አገልግሎቱ ገሉጿል።

አሸባሪው አካል በታላቁ የኮሪያ መሪ ላይ የቦምብ ጥቃት ለማድረስ ያሰበው በቅርቡ የታየውን የወታደራዊ ትዕይንት ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች እንደነበር ለማወቅ ተችሏል ሲል የዜና ወኪሉ አስታውቋል።

በሰሜን ኮሪያ የዜና አገልግሎት በኩል የቀረበው ዘገባ እንደሚያመለክተው፣ የግድያ ሙከራው በሰሜን ኮሪያ ዜጋ ሊፈጸም ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ባዮኬሚካል ንጥረ ነገር እና ራዲዮ አክቲቭ መርዛማ ንጥረነገሮችን መጠቀምን የጨመረ ነበር ሲል  ገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ በታላቁ መሪ ኪም ጆን ኡን ላይ ሊደርስ ታቅዶ ነበር ብላ ያቀረበችውን የግድያ ሙከራ፣ እስካሁን በነጻ ምንጭ አልተረጋገጠም። የደቡብ ኮሪያ የጸጥታ አገልግሎት በበኩሉ ሊደረግ ታቅዶ ነበር ስለተባለው የግድያ ሙከራ የሚያውቀው ነገር እንደለሌም ገልጿል። ሆኖም ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያውን መሪ መግደልን ጨምሮ ሌሎች እቅዶች እንዳሉ ገልጸዋል።

የሰሜን ኮሪያ የዜና አገልግሎት ሴራው መቼ እንደተጋልጠና በቁጥጥር ስር እንደዋለ የገለጸው ነገር የለም።