ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ጉብኝትን በማድረግ ላይ የነበሩት የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብደላሂ ረቡዕ በሞቃዲሾ ከተማ በአንድ ሚኒስትር ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ ጉብኝታቸውን አቋረጡ።
ረቡዕ የሶስት ቀን ጉብኝትን ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተው የነበሩት ፕሬዚደንቱ ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመምከር እቅድ እንደነበራቸው ታውቋል።
በአንድ ቀን ቆይታቸው ረቡዕ ምሽት በጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ለመወያየት ይዘውት የነበረው እቅድ ግን ሳይካሄድ ቀርቷል።
ረቡዕ ዕለት በሞቃዲሾ ከተማ በተተኮሰ ጥይት የሃገሪቱ የግንባታ ሚኒስትር የነበሩት ኦባል አብዱላሂ ሼክ ሲራጅ መገደላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። የሚኒስትሩን መገደል ተከትሎ በአዲስ አበባ የነበሩት ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብዱላሂ ጉብኝታቸውን አቋርጠው ሃሙስ ወደ ሞቃዲሾ ማቅናታቸው ታውቋል።
ፕሬዚደንቱ በሚኒስትሩ የቀብር ስነስርዓት ላይ ለመታደም ሲሉ ጉብኝታቸውን ለማቋረጥ እንደወስኑ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ይሁንና ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብደላሄ ጉብኝታቸውን በድጋሚ ያካሄዱ አያካሄዱ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያም ሆነ በሶማሊያ በኩል የተሰጠ መረጃ የለም።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ በተናጠል አሰማርታ የምትገኘው የወታደሮች ጉዳይ በፕሬዚደንቱ ጉብኝት ወቅት ዋነኛ መወያያ አጀንዳ ብሎ መያዙን ራዲዮ ፍራንስ በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ዘገባ አመልክቷል። አዲሱ የሶማሊያው ፕሬዚደንት ኢትዮጵያ ባሰማራቻቸው ወታደሮች ደስተኛ አለመሆናቸው በሰፊው ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ ይኸው አቋማቸው ለድል እንዳበቃቸው የሶማሊያ ባለስልጣናት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር ካሰማራቻቸው ወደ አራት ሺ አካባቢ ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቀ የተናጠል ወታደሮችን በተለያዩ የሶማሊያ ግዛት አሰማርታ ትገኛለች።
ይሁንና ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ አብዛኞቹ ወታደሮች ከቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው የወጡ ሲሆን የተለቀቁ ቦታዎች በታጣቂ ሃይሉ አልሸባብ ቁጥጥር ስር መግባታቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ ወደ 22ሺ አካባቢ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሃገሪቱ ተሰማርተው ቢገኙም ታጣቂ ሃይሉ አሁንም ድረስ እያደረሰ ካለው ጥቃት ጎን ለጎን አብዛኛውን የሶማሊያ ግዛት ይዞ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
በታጣቂ ሃይሉ እንቅስቃሴ ስጋት ያደረባት አሜሪካ በበኩሏ በአልሸባብ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኗን አስታውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከሶማሊያው ፕሬዚደንት ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው ከሶማሊያ የፌዴራል ዕውቅና ውጭ ከፑንትላንድም ሆነ ከሶማሊላንድ እንደማይገኛኙ አስታውቋል።