ሚያዝያ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እንደ አሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዘገባ ከሆነ ለምስራቅ አፍሪካ በየአመቱ ይመደብ ከነበረው አጠቃላይ እርዳታ የ30.8% ቅናሽ መደረጉንና ይህም በሚቀጥለው በጀት አመት 2017/18 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቋል። በዚሁ መሰረትም ከፍተኛ ቅናሽ ከተደረገባቸው አገሮች መካከል የኢትዮጵያው 131.2 ሚሊዮን ዶላር ከፍተኛው ሲሆን ፣ ዩጋንዳ 67.8 ሚሊዮን ዶላር፣ ሩዋንዳና ታንዛንያ እያንዳንዳቸው 50.7 ሚሊዮን ዶላር፣ኬንያ በበኩሏ 11.78 ሚሊዮን ድላር ስታጣ ደቡብ ሱዳንና ብሩንዲ እንደየ ቅደም ተከተላቸው 10.6 እና 9.4 ሚሊዮን ዶላር ተቀናሽ እንደሚደረግባቸው ታውቋል።
ይሁንና ጎረቤት አገር ሶማሊያ በአዲሱ እቅድ የ 36.1 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ እንደምታገኝ ሲገለጽ ፣ ባለፉት 2 ዓመታት ኢትዮጵያ፣ታንዛንያ፣ኬንያ እና ናይጄሪያ ከአሜሪካ መንግስት ከአፍሪካ ከፍተኛውን እርዳታ ያገኙ እንደነበር ተጠቁሟል::
እንደ አሜሪካው የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ገለጻ ከዚህ በኋላ የእርዳታ ትኩረታቸው የሚሆነው ጽንፈኞችን ለመዋጋት የሚሰሩትን፣ የህግ የበላይነትን ለማሻሻል የሚተጉትንና የግል ሴክተሩን ማሰልጠንና ማገዝ እንደሚሆን ጠቁመዋል።