ሚያዝያ ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ተመድ በኢትዮጵያ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ታዳጊ ህጻናት ተጎጂዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ በኩል የ3 ሚሊዮን ዩሮ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የተገኘውም እርዳታ ክፉኛ ለተጎዱ ህጻናት ህይወት ለማዳን እንደሚውልም ድርጅቱ አስታውቋል። ከፍተኛ ድርቅን ተከትሎ ርሃብ በተከሰተባቸው የአፋር፣ ሶማሊያ፣ ኦሮምያ እና ደቡብ ክልሎች ነዋሪዎች በቂ የሆነ የጤና እና የንጹህ ውሃ አቅርቦት እንደማያገኙ ተመድ ገልጿል። በዚሁ ምክንያትም በያዝነው ዓመት ብቻ ቁጥራቸው ከ303 ሽህ በላይ የሚሆኑ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።
በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ሚስ ጊልያን ማልሶፕ የአውሮፓ ህብረት ላደረገው ወቅታዊና ወሳኝ እርዳታ አመስግነው እርዳታው በድርቁ የተጎዱትን ህጻናት ህይወት ለመታደግ ይውላል ብለዋል። የአገሪቱንም የጤና ሁኔታ ለማሻሻል ድርጅታቸው ሲሰራ መቆየቱን እና የምግብ ድጋፍም እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚኖሩትን አርብቶ አደሮች የአፋር እና ሶማሊያ ነዋሪዎችንም ድርጅታቸው ሲያግዝ መቆየቱንም አስረድተዋል።
የህጻናቱን ስቃይና ሞት ለመቀነስ አቅም ማሳደግ ተገቢ መሆኑንና ችግሮች ሲፈጠሩም ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ አፋጣኝ መፍትሄ ማፈላለግ ያስፈልጋል ሲሉ ሚስ ጊልያን ማልሶፕ አሳስበዋል።