“ኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲሱ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አልበም በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከተጠበቀው በላይ መሆኑን የአርቲስቱ የቅርብ አማካሪዎች በተለይ ለኢሳት ገለጹ።

ሚያዝያ ፳፭ ( ሃያ አምስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመጀመሪያው ዙር የታተመው 500 ሺህ ኮፒ በቂ ላይሆን ይችላል የሚል ሥጋት በማሳደሩና በበርካታ አፍሪካ ሀገሮች ካሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተጨማሪ ጥያቄ በመቅረቡ ሁለተኛ ዙር ሕትመት መቀጠሉን አስተባባሪዎቹ አስረድተዋል።
አልበሙ ከወጣበት ማክሰኞ ከቀኑ 6 ፡00 ሰዓት ጀምሮ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው ሕዝብ ወደ ሲዲ መደብሮች በመትመሙ አከፋፋዮችና ነጋዴዎች በአዲስ አበባ ለህዝብ ግልጽ ሆነው በሚታዩ ስፍራዎች ላይ ድንኳኖችን በመዘርጋት ለመሸጥ መገደዳቸውን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
አከፋፋዮች የተከራዩዋቸው ከመርካቶና ከአውቶቡስ ተራ ወደ ክፍለ ሀገር የሚሄዱ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችም የአርቲስቱን ፖስተር ለጥፈውና አልበሙን ይዘው በሰልፍ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ከተሞች ሲጓዙ ልዩ ሀገራዊ በአል የሚከበር ይመስል እንደነበር የአውቶቡስ ተራ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በትናንትናውና በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የቴዲ አፍሮን ፖስተር በለጠፉ ሚኒባስ ታክሲዎች ደምቀው ታይተዋል። ይሁንና በዛሬው ዕለት የአርቲስቱን ፖስተር ለጥፈው ሙዚቃውን በሞንታርቦ እየሰሙ ሲዞሩ የነበሩ ሁለት ሚኒባስ ታክሲዎች ፣“ ሕዝብ ለማመላለስ እንጂ ለመቀስቀስ ከመስተዳድሩ ፈቃድ አልተሰጣችሁም “ተብለው በፖሊስ መታሰራቸው ታውቋል።
እንደ አስተባባሪዎቹ ገለጻ አዲሱ የቴዎድሮስ አልበም እስከዛሬ ድረስ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ከተሞች መድረሱና በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸጠ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በሁሉም የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት እስከ ነገ ድረስ ይዳረሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በአከፋፋዮችና በነጋዴዎች በሀገርና በውጪ ሀገራት እየተደረገ ካለው ሽያጭ በተጨማሪ በኢንተርኔት የሚደረገው የኦንላይን ሽያጭም ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪዎቹ፣ የዓለማችንን አርቲስቶች አልበም በኢንተርኔት በመሸጥ የሚታወቀው ሲዲ ቤቢ የተሰኘው ገጽ ላይ ሳይቀር እስካሁን ከፍተኛ ሽያጭ ያከናወነው አዲሱን የቴዲን ኢትዮጵያ አልበም እንደሆነ በገጹ ላይ ይፋ ማድረጉን አስረድተዋል።
ይህም የውጪ ገበያ በሚያካሂድ ገጽ ሳይቀር የአንድ ኢትዮጵያዊ አርቲስት ሥራ ቀዳሚ ሆኖ መገኘቱ ለአርቲስቱም ሆነ ለአገሩ የመጀመሪያው ሪከርድ እንደሆነ አማካሪዎቹ አብራርተዋል።
ሌላው ይህን አልበም ልዩና ታሪካዊ የሚያደርገው፤ ሕትመቱ የተካሄደው በ50 ሚሊዮን ብር በዱከም በተገነባውና “ ቆሊያ ማኑፋክቸሪንግ” በተሰኘው አገር በቀል ሲዲ አምራች ፋብሪካ መሆኑ ነው ሲሉም አማካሪዎቹ ተናግረዋል።
በተለይ ኢትዮጵያና አጼ ቴዎድሮስ የተሰኙት በአልበሙ የተካተቱ ሙዚቃዎች በጎሳ ፖለቲካ የቆሰለውን የአብዛኛውን ሕዝብ ስሜት ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ በኩል ጉልህ ሚና መጫዎታቸውን ራዛቢዎች ይገልጻሉ።
የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ሳይቀሩ ምርቶቻቸውን በአርቲስቱ ስም መሰየም የጀመሩ ሲሆን፤ የሻምፖና የሳሙና አምራቾች በምርታቸው ላይ የአርቲስቱን ምስሎች ለጥፈዋል።
በማህበራዊ ሚዲያውም በኩል ይህ የቴዎድሮስ ካሳሁን የአዲስ አልበም ሊወጣ ነው ብሎ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ሳምንታት ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።