ኢሳት (ሚያዚያ 24 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በትልልቅ ድርጅቶች ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ማምጣቱ ተገለጸ። በዚህም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አጠቃላይ ገቢው ባለፉት ዘጠኝ ወራቶች በ1.5 ቢሊዮን ብር መቀነሱን አስታወቀ።
ይኸውም መንግስታዊ ተቋም በዘጠኝ ወራቶች ውስጥ 14.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰባሰብ ቢያቅድም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት 11.8 ቢሊዮን ብር አካባቢ ብቻ ማግኘቱን የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለኢንተፕራይዙ የስራ አመራር ቦርድ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
ሃገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት በድርጅቱ ላይ ካስከተለው የገቢ መቀነስ በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ላይም ቅናሽ እንዲታይ ማድረጉን የድርጅቱ ሃላፊዎች ማስረዳታቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የኢንተርፕራይዙ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መስፍን ተፈሪ ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ቅድሚያ የሚሰጠው ለተመረጡ ዘርፎች መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ ሌተር ኦፍ ክሬዲት (L.C)) በበቂ ደረጃ መክፈት ባለመቻሉ ወደ ሃገሪቱ የሚገባ ዕቃ በመጠን ቅናሽ ሲያሳይ መቆየቱን አክለው አስታውቀዋል።
ይኸው የንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በኢንተርፕራይዙ ገቢ ላይ ቅናሽ እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ከሃላፊው ለመረዳት ተችሏል።
ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተለያዩ መንግስታዊና የግል የንግድ ተቋማት ዘንድ የገቢ መቀነስ እንዲያጋጥም ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት ይህንኑ እየተባባሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ሲባል የመካከለኛ ምስራቅ ሃገራት ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያስቀምጡ መደረጉን ከወራት በፊት መግለጻቸው ይታወሳል።
ይሁንና የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ አሁንም ድረስ መቀጠሉን የሚናገሩት ባለሃብቶች የውጭ ምንዛሪን ለማግኝነት ከስድስት እስከ 8 ወራቶች እንደሚጠብቁ ይናገራሉ።
የችግሩ መባባስን ተከትሎ መንግስት አዲስ መመሪያን በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡም ሆነ ከኢትዮጵያ የሚወጡ መንገደኞች በእጃቸው የሚገኝ የውጭ ሃገር ገንዘብና ጌጣጌጦች እንዲያስመዘግቡ መደረጉ አይዘነጋም።
የአለም ባንክና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በበኩላቸው መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን እንዲሁም ብር ከዶላር ጋር ያለውን የመግዛት አቅም እንዲቀንስ አሳስበዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋማቱ ያቀረቡት ሃሳብ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚበልጥ ነው በማለት የቀረበውን ሃሳብ እንዳማይቀበሉት ምላሽን ሰጥተዋል። አንድ የአሜሪካን ዶላር በባንኮች ከ23 ብር በታች በመመንዘር ላይ ሲሆን፣ በጥቁር ገበያ ግን አንድ ዶላር ከ27 ብር በላይ በሆነ መጠን እንደሚቀየር ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።