በቅርቡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረበው ሪፖርት “ተዓማኒነት” የጎደለው ነው ሲል አንድ ተቋም ገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 23 ፥ 2009)

መቀመጫውን በቤልጂየም ያደረገ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የቀረበን ሪፖርት “ተዓማኒነት” የጎደለው ነው ሲል አጣጣለው።

ይኸው Unrepresented Nation and Peoples Organization የሚል መጠሪያ ያለው ተቋም በኮሚሽኑ ሪፖርት የተደረገው የሟቾች ቁጥር በትክክለኛ ያልተቀመጠና በገለልተኛ ያልተከናወነ ነው በማለት ምርመራው በገለልተኛ አካል እንዲካሄድ ጥሪውን አቅርቧል። በኦሮሚያ፣ አማራና የደቡብ ክልሎች የተካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን በተመለከተ ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀረበው ኮሚሽኑ 669 ሰዎች መገደላቸውን መግለፁ ይታወሳል።

ይሁንና የሪፖርቱ ይፋ መደረግን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በንጹሃን ሰዎች ላይ የፈጸሙት ድርጊት ከነምስክሮች ተሟልቶ መቅረብ እንደነበረበትም አመልክቷል።

ኮሚሽኑ ያካሄደው ምርመራ ገና ከጅምሩ ጥያቄ የነበረበት ነው ያለው የቤልጅየሙ ተቋም፣ የምርመራ ውጤቱ የመንግስት ባለስልጣናት የጸጥታ አባላትን ድርጊት ለመሸፈን ያለመ መሆኑንም አክሎ ገልጿል። የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ በአብዛኛው ተመጣጣኝ ነበር ተብሎ መቀመጡ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው መንግስት ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዳይካሄድበት የወሰደው አቋም ያመጣው ነገር ቢኖር ድርጊቱ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገ ነው ሲል ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል። በቅርቡ ለፓርላማ ሪፖርቱን ያቀረበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለ669 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የጸጥታ ሃይሎች ዕርምጃ በአብዛኛው ተገቢና ተመጣጣኝ የነበረ ነው ሲል መግለጹ ይታወሳል። ከቀደመው ሪፖርት ጋር በአጠቃላይ የሟቾቹ ቁጥር 745 እንደሆነም ገልጿል።

የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ዎች እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች በሪፖርቱ የቀረበው የሟቾች ቁጥር ሊበልጥ ይችላል ሲሉ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት አየጠየቀ ይገኛል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የቀረበውን አለም አቀፍ ጥሪ እንደማይቀበለው አስታወቆ ጉዳዩ የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። አሜሪካ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ሌሎች አለም አቀፍ አካላት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ በገለልተኛ አካል መጥራት እንዳለበት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄን አቅርቦ ከመንግስት ምላሽን የተነፈገው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊው ዘይድ ራ’አድ አል ሁሴን ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ የሶስት ቀን ጉብኝት ጉብኝት እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

ሃላፊው በሰብዓዊ መብት ጉዳዩች ዙሪያ ከመንግስትና ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት እንዲሁም ከሲቪል ማህበረሰብና የፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።