የደሴ ከተማ በተከታታይ ጎርፍ እየተጠቃች መሆኗን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪዎቹ ለኢሳት እንደገለጹት በተለይ ከሰሞኑ የሚጥለው ተከታታይ ዝናም እየስከተለ ባለው ከባድ ጎርፍ ቤታቸው በመጥለቅለቁ በርካታ ንብረት እየወደመባቸው ይገኛል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ለአካባቢው መስተዳድር አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጊዜያዊም ሆነ ዘላቂ ምላሽ ሊያገኙ አለመቻላቸውን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ አንዳንዶች ጎርፉ ክፉኛ ቤታቸው ዘልቆ በመግባቱ መኖሪያቸውን ጥለው በየዘመዶቻቸው ቤት መጠለላቸውን ይገልጻሉ።
ከዚህም ባሻገር የመኪና መንገዶች ሁሉ ጎርፉ በሚያመጣው ደለል በመዘጋታቸው በታክሲና በሌሎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ እክል መፈጠሩንም ባለታክሲዎች ገልጸዋል።ከጦሳ እና በከተማዋ ዙሪያ ካሉት ተራሮች በጎርፉ አማካይነት እየወረደ ላለው ደለል አስቸኳይ መፍትሔ ካልተፈለገለት ከፍ ያለ ችግር መፈጠሩ እንደማይቀር ጾፌሮች ያስጠነቅቃሉ።
በጎርፍ ምክንያት ከቤታቸው በመፈናቀል በዘመድ ቤት የተጠለሉ የከተማዋ ነዋሪዎችም የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።