ከፊ ሚነራል የአንድ ሚሊዮን ፓውንድ ስትርሊግን እሴት ታክስ ተመላሽ ከመንግስት መቀበሉን ገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 20 ፥ 2009)

በኦሮሚያ ክልል የወርቅ ማውጣት ስራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ የሚገኘው ከፊ ሚነራል ኩባንያ የአንድ ሚሊዮን ፓውንድ ስተርሊንግ (ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ) የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) ተመላሽ ከመንግስት መቀበሉን አርብ አስታወቀ።

በለንደን አለም አቀፍ የአክሲዮን ንግድ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ይኸው ድርጅት የቱሉ ቆጲ  ፕሮጄክቱ ከሌላ ኩባንያ በተረከበ ጊዜ ያለአግባብ የድርጅቱን የቫት ክፍያ እንድፈጸም ተደርጊያለሁ ሲል ከወራት በፊት ቅሬታውን አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

አለም አቀፍ የማዕድን ኩባንያው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በአጠቃላይ 73 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ እንድከፍል አድርጎኛል በማለት መንግስት ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርግለት ሲያግባባ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።

ኩባንያው ሰሞኑን የወርቅ ማውጣት ስራውን እንዲጀምር ማስታወቁን ተከትሎ ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት አካል የ30 ሚሊዮን ብሩን ተመላሽ እንዲያደርጉለት አስታውቋል።

ቀሪው 43 ሚሊዮን ብር ደግሞ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ተመላሽ እንዲያደርግለት ማረጋገጫ ማግኘቱን ኩባንያው አክሎ ገልጿል።

መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው ከፊ ሚኒራልስ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ለሚያካሄደው የወርቅ ማውጣት ስራ ቁጥራቸው ያልተገለጸ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር ከመንግስት ጋር መስማማት መደረሱን ሃሙስ ይፋ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁንና መንግስትም ሆነ ኩባንያው ምን ያህል ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደሚነሱና የሚከፈላቸውን ካሳ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ከመንግስት ተመላሽ የተደረገለትን ገንዘብ ለዚሁ የወርቅ ማውጣት ስራ መልሶ እንደሚጠቀመው የኩባንያው ሃላፊ ሃሪ አዳምስ ለድርጅቱ የአክሲዮን ድርሻ አባላት ባሰራጩት መረጃ አስታውቀዋል።

ከአርብ ሚያዚያ 20 ፥ 2009 አም ጀምሮ የከፊ ሚኒራልስ ተወካዮች በምራብ ወለጋ የገንጂ ወረዳ ስር በሚገኙ የቃቢ ጉራቻ ቢቂልቱ አንቆሬ መንደሮች የፕሮጄክት ምልከታ እንደሚያደርጉም ለመረዳት ተችሏል።

የ20 አመት ሙሉ ኮንትራት ከመንግስት ጋር የተፈረመውን ይኸው ኩባንያ ከሁለት አመት በፊት በሌላ ኩባንያ ተይዞ የነበረውን ፕሮጄክት መረከቡን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ይሁንና የቀድሞ ኩባንያ ለፕሮጄክቱ ገንዘብ ማሰባሰብ ባለመቻሉ ማስተላለፉን አካሄዷል።

የከፊ ሚኒራልስ የስራ ሃላፊዎች ለዚሁ ፕሮጄክት ስራ ማስጀመሪያ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከባለሃብቶች መሰብሰቡንና፣ የአለም አቀፉ ባለሃብቶች ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።