የተመድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል ሃላፊ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

ሚያዝያ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ዋና አዛዥ የሆኑት ዘይድ ራድ አል ሁሴኒ በመጪው ሳምንት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ድርጅቱ አስታውቋል።

የእሳቸው ጉብኝት ከመካሄዱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያለቁበት ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ጥያቄ፣ የኢህአዴግ አገዛዝ ውድቅ እንዳደረገው አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መናገራቸው ይታወሳል።
ተመድ በመግለጫው ላይ እንዳለው ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ከአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ይወያያሉ።
በገዥው ፓርቲ የሚደገፈው ራሱን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብሎ የሚጠራው ተቋም አደረኩት ባለው ምርመራ ፣ ህዝባዊ አመጹ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ በነበራባቸው ሁለት ወራት ውስጥ 63 የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ በድምሩ 669 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ገልጿል። ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ ከተቀጣጠለበት ከ2015 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በመንግስት ታጣቂዎች የተገደሉት ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር ከዚህ በላይ ይሆናል ሲሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አቶ ሃይለማርያም የተመድን የሰብአዊ መብት ሃላፊ መጋበዛቸው፣ የገዢውን ፓርቲ ባለስልጣናት በተወሰደው እርምጃ መደናገጣቸውን የሚያሳይ ነው። የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ እውነተኛው አሃዝ ይፋ እንዲሆንና አጥፊዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ሲወተውቱ ቆይተዋል።