በሶማሊያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የኬንያ እና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከመጠን በላይ ሃይል ተጠቅመው ዜጎችን መግደላቸውን ሪፖርቶች አጋለጡ

ሚያዝያ ፳ ( ሃያ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኬኒያ እና ኢትዮጵያ ወታደሮች አልሸባብን ለማደን በሚል ምክንያት ድንበር አቆራርጠው ወደ ሶማሊያ ግዛት በመግባት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከመጠን በላይ የሆነ የሃይል እርምጃዎችን መውሰዳቸውን በሶማሊያ የተሰማሩ የረድኤት ድርጅቶች ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ባቀረቡት ሪፖርቶች አጋልጠዋል።

በሶማሊያ ጌዶ ግዛት ውስጥ ከ2015 እ.ኤ.አ. ጀምሮ የኬንያ አየር ሃይል፣ አርብቶ አደሮች በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ድንበር ተሻግሮ የአየር ጥቃቶችን ፈጽሟል። የኬንያ የዱር እንስሳት ጥበቃ የድንበር ቅኝት በሚያደርግበት ወቅትም ከሕግ አግባብ ውጪ ሰላማዊ ዜጎችን ይገድላሉ፣ ያታሰራሉ ሰቆቃዎችንም ይፈጸሙባቸዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በበኩሉ ድንበር በመሻገር አርብቶ አደሮች ላይ ሰብዓዊ መብታቸውን የጣሰ ድርጊቶችን ይፈጽማል። በኢትዮ-ሶማሌ ድንበር አቅራቢያ ”አረንጓዴው ዞን’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ጦር አባላት በነዋሪዎች ላይ የተለያዩ የወሲብ ጥቃቶችን ፈጽመዋል። እንደ ሪፖርቱ መግለጫ ወታደሮቹ ሴቶችን በግዳጅ ይደፍራሉ፣ የጅምላ የወሲብ ጥቃት ይፈጽሙባቸዋል። ይህንን ተከትሎ ሴቶች ለተለያዩ አካላዊ ጉዳቶች ተደርገዋል።

የኬንያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ጆሴፍ ኦዎዝ ”የቀረቡብን ውንጀላዎች በሙሉ በብዙ መልኩ ከእውነት የራቁ ናቸው። እኛ ኢላማችን የአልሸባብ አሸባሪዎች ላይ ብቻ ነው። መቼም ሰላማዊ ዜጎች፣ ሕንጻዎች እና የውሃ ጉድጓዋዶች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አንፈጽምም። በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ በመከሰቱ ነዋሪዎች ውሃ ፍለጋ ከቤት እንስሳት ጋር በቡድን ይፈልሳሉ። እነደዚህ ዓይነት ስፍራዎች ላይ ተኩስ አንከፍትም። የዱር አራዊት ጥበቃ መስሪያ ቤትም ድንበር ተሻግሮ ጥቃቶችን አያደርስም።” በማለት የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል። በኢትዮጵያ በኩል ግን እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠም።
ነገር ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ስለሚፈጸሙባቸው ሰቆቃዎች ምስክርነታቸው መስጠታቸውን ሪፖርቱ አትቷል። በጌዶ ግዛት ሊኮኒ መንደር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ አቶ መሀመድ ኑር ኦስማን የተባሉ አንድ የአገር ሽማግሌ ”የኬኒያ አየር በተደጋጋሚ ጊዜያት በግጦሽ በተሰማሩ አርብቶ አደሮች እና በቤት እንስሳት ላይ ጥቃቶችን ያደርሳሉ። ነዋሪዎች በድርቁ ምክንያት መኖሪያ ቀያቸውን በመተው ዝናብ ወደሚጥልባቸው አካባቢዎች ይፈልሳሉ። የኬንያ ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖች ግን ከጉዞዋቸው ያስተጓጉሏቸዋል” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

አክለውም ”በቅርቡ ከሰባት ቀናት በፊት አንድ የአየር ጥቃት በመንደራችን ላይ ተፈጽሟል። ደመናን የሚከተሉ ሰላማዊ ዜጎች ወደ አካባቢው እየመጡ ነበር። በእነሱ ላይ ጥቃት ተፈጸመባቸው አንድም ሰው አልሞተም ፍየሎች እና ግመሎችን ጨምሮ የተለያዩ የቤት እንስሳት ግን አልቀዋል።”ሌላው በኢትዮ ሶማሌ ድንበር ነዋሪ የሆኑ የዓይን እማኝ አቶ ሃሰን መሃመድ ሙክታር በበኩላቸው ”ታናሽ እህቴ ሩቂያ ከ15 ወራት በፊት ከባርዬ ከተማ በልዩ ፖሊስ ጦር አባላት ታፍና ተወስዳ ታስራለች። ባለቤትሽ የአልሸባብን ተልእኮ ለማስካት 100 ዶላር ተቀብሏል የሚል ምክንያት አልባ ክስ ቀርቦባታል” ብለዋል።

አዲስ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ሁለቱም አገራት ከአሜሶም ውጪ የሆነ ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ አስገብተዋል። እኒዚህ ከአሜሶም እውቅና ውጪ የተሰማሩ ወታደሮች ከአሜሶም ተልእኮ እና ዓላማ ውጪ የሆኑ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት የሌላቸው የተለያዩ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን በሶማሊያንዊያን ዜጎች ላይ ይፈጽማሉ።
በኢትዮጵያ በ2007 እ.ኤ.አ. ልዩ ፖሊስ ተብሎ የኦጋዴን ነጻነት ግንባር ለመዋጋት የተቋቋመው ሲሆን፣ በኦጋዴን ነዋሪዎች ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንደሚፈጽሙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን አቅርበዋል።
ሪፖርቱ በማጠቃላያው ላይ የሰብዓዊ እርዳታውን በተገቢው መንገድ በማድረስ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ እንዲቻል የአደጋ ቀጠና የሆኑት አካባቢዎች ከማንኛውም ተጽእኖዎች ነጻ እንዲሆኑ ሲል ጠይቋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሶማሊያ የተሰማሩ ሶስት መንግስታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ረድኤት ድርጅቶች ህብረት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ”በጦርነት እና በሃብ የተጎዱትን ተፈናቃዮችን ከለላ እንስጥ” በሚል መሪ ቃል በጋራ ሪፖርቱን አጠናቅረው ማቅረባቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።