ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2009)
ታዋቂው የህዋ ሳይንስ ምሁር ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ለገሰ ወትሮ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
በአስትሮ ፊዚክስ ሙያ የላቀ አስተዋጽዖ ያደረጉት ዶ/ር ለገሰ ወትሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በመሆን አገልግለዋል። የተለያዩ የአለም አቀፍ ሽልማቶች ባለቤትም ነበሩ።
በኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ እንዲጎለብት የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ዶ/ር ለገሰ ወትሮ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበርን ከመሰረቱት ምሁራን እና የሙያ አፍቃሪዎች አንዱ ነበሩ። የህዋ ሳይንስ ምሁርና የአለም አቀፍ የስነፈለግ የህብረት አባል እንደነበሩም የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ዶ/ር ለገሰ ወትሮ በኤፍ ኤም አኢድስ 97.1 ሬዲዮ ላይ ሳምንታዊ የህዋ ሳይንስ ፕሮግራም እራሳቸው አዘጋጅተው በመቅረብ ይታወቁ ነበር።
በኋላም የራሳቸው የህዋ ሳይንስ ፕሮጄክቶች ይዘው ከአፍሪካና ከሌሎች የአለም መሰል ተቋማት ጋር በመስራት መስኩን ለማሳደግ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል።
ዶ/ር ለገሰ ወትሮ የልብ ህመምተኛ እንደነበሩና በቤታቸው ውስት በተኙበት ድንገት ህይወታቸው አልፏል። የቀብር ስነስርዓታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ወፓውሎስ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።