የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ወደጎንደር ከተማ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰበ

ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2009)

በጎንደር ከተማ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን የቦምብ ፍንዳታ ተከትሎ አሜሪካ ዜጎቿ ወደ አካባቢው በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ ዕርምጃን እንዲስወዱ ሃሙስ አሳሰበ።

በተያዘው ወር ብቻ አራት የእጅ ቦምቦች ጥቃት መድረሱን ያረጋገጠው በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ፣ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ከሁለት ቀን በፊት በአንድ የቱሪስቶች ማረፊያ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ማስረዳታቸውን ይታወሳል።

በተደጋጋሚ እየደረሰ ባለው በዚሁ የቦምብ ፍንዳታ ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎች ጉዳት እንደደ ረሰባቸው የአሜሪካ ኤምባሲ ድርጊቱን አስመልክቶ በድረ-ገጹ ባሰፈረው የጉዞ ማሳሰቢያው አስፍሯል።

በጎንደር ከተማ ያሉም ሆነ ወደ ስፍራው ለመሄድ ፍላጎት ያላቸው አሜሪካውያን ወቅታዊ ሁኔታውን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አካባቢው በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ ኤምባሲው አሳስቧል።

በሃገሪቱ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

ባለፈው ሳምንት የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመሳሳይ ማሳሰቢያን በማውጣት ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ ዕርምጃን እንዲወስዱ ሲያሳስብ ቆይቷል።

የአሜሪካና የብሪታኒያ መንግስታት በጎንደርና በባህር ዳር ከተሞች የተፈጸሙ የፍንዳታ ጥቃቶችን በማስመልከት ለዜጎቻቸው ማሳሰቢያን ቢያሰራጩም የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽን ከመስጠት ተቆጥቧል።

ባለፈው አመት በአማራ ክልል ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተለያዩ የክልሎች ቦታዎች አለመረጋጋት መቀጠሉን ነዋሪዎች ለኢሳት ሲገልፅ ቆይተዋል።

ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ባለፈው ወር ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት ስማቸውን ባልጠቀሳቸው የሃገሪቱ ቦታዎች አለመረጋጋት መቀጠሉን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው።