በህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት የተገደሉት የሟች ቤተሰቦችን ካሳ ለመስጠት ምዝገባ ተጀመረ

ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2009)

በመንግስት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ የወጣውን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢ የሟች ቤተሰቦችን ካሳ ለማግኘት ተመዝገቡ የሚል እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል። በዚህም የፌዲራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አዛዦችን ከተጠያቂነት ነጻ በማድረግ የአካባቢ ሚሊሺያ ታጣቂዎችና ሃላፊዎችን ለመክሰስ ጠበቃ እንደተቀጠላቸውም ተነግሯቸዋል።

ከባህር ዳር ለኢሳት በደረሰው መረጃ መሰረት በሃምሌ 1 ፥ 2008 ብቻ ከመቶ ሰዎች በላይ እንደተገደሉበት ሲገለጽ በቆየው ባህርዳር ከተማ አንዳንድ የሟች ቤተሰቦችን ማነጋገርና መመዝገብ የተጀመረው  ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ሲሆን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የአካባቢ ሚሊሺያዎች እንዲሁም በወቅቱ ታስረው እስካሁን ያልተፈቱ ወጣቶች በግድያውም ሆነ በውድመቱ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች ተነግሯቸዋል።

የአካባቢ ሚሊሺያዎች ከአቅም በላይ ሃይል ተጠቅመዋል በማለት በየቤቱ እየዞሩ ሰለባዎቹን ቅጽ በሚያስሞሉ የብአዴን/ኢህአዴግ አባላት እየተናገሩ ሲሆን፣ የሟች ቤተሰቦች በፍ/ቤት በምስክርነት እንዲቀርቡም ተጠይቀዋል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአንዳንድ በስም በጠቀሳቸው ቦታዎች የጸጥታ ሃይሎች ከመጠን ያለፈ ሃይል ተጠቅመዋል ባላቸው ቦታዎች ሁሉ ይኸው ሁኔታ እንዲቀጥል የተጠበቀ ሲሆን፣ ዕርምጃውን በበላይነት የሚመሩትና ግድያውን በተዋረድ የሚያስፈጽሙ ሃላፊዎች ከተጠያቂነት ነጻ በማድረግ የቀጠለው ሂደት በየአካባቢው  ለተፈጸሙ ግድያዎች የአካባቢው ተወላጆችን ብቻ ተጠያቂ በማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን መረዳት ተችሏል። ሆኖም ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት መስከረም 28 ፥ 2009 ጀምሮ የክልሎች ጸጥታ ሙሉ በሙሉ በእዚሁ ዕዝ ስር የወደቀ ሲሆን፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችን በበላይነት የመሩትና ዕርምጃውን ያስወሰዱት የኮማንድ ፖስቱን ሃላፊዎች የያዙት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ታጋዮች የነበሩት የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ሃላፊዎች መሆናቸውም ሲገለጽ ቆይቷል።

በመንግስት የተቋቋመውና በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃት አባል በዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር የሚመራው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሳምንት በፊት በፓርላማ ባቀረበው ሪፖርቱ ከሃምሌ 2008 እስከ መስከረም 2009 ድረስ ብቻ ባሉት ሶስት ወራት በኦሮሚያ ክልል 4 ብቻ 462 ሲቪሎች ሲገደሉ በአማራ ክልል ደግሞ 110 ሲቪሎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ሰኔ 2 ፥ 2008 ይኸው መንግስት የተቋቋመውና በህወሃቱ አባል በዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚያብሄር የሚመራ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከህዳር 2008 እስከ ሰኔ 2008 በኦሮሚያ ክልል 173 ሰዎች መገደላቸውን ለፓርላማ ማስታወቁም አይዘነጋም። በጠቅላላ በመንግስታዊ ተቋም ሪፖርት መሰረት 60 ያህል የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ከህዳር 2008 እስከ መስከረም 2009 አም ድረስ 745 ሰዎች መገደላቸውንና 1562 ደግሞ መቁሰላቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከወጣበት ከመስከረም 28 ፥ 2009 ጀምሮ ባለፉት 7 ወራት የተካሄደ ግድያዎችም በተመለከተ የኮሚሽኑ ሪፖርት አላካተተም። መስከረም 2009 ላይ ቆሟል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎች በቁጥር ብቻ ሳይሆን በዘግናኝነታቸው የከፉ እንደሆኑ ይጠቀሳል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ በሁለተኛው ቀን መስከረም 30 ፥ 2009 በምስራቅ አርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ ጎቤሳ 01 ቀበሌ በአንድ ቤት ሶስት ወንድማማቾች በታጣቂዎች የተገደሉበት ድርጊት በወላጅ አባታቸው አንደበት በአሜሪካ ድምፅ ላይ መቅረቡ ይታወሳል።

አቶ ጀማል ሃሰን ለቪኦኤ እንደተናገሩት መስከረም 30 ፥ 2009 የተገደሉት ሶስቱ ልጆቻቸው መርሃቡ ጀማል፣ ቶላ ጀማል እንዲሁም አብዲሳ ጀማል ሲሆኑ ዕድሚያቸው 26 ፥ 24 እና 25 እንደሆነም ተመልክቷል። የእነዚህን ሶስት ወድንማማቾች ግድያን ጨምሮ በ7 ወራት ውስጥ ስለተፈጸመው ድርጊት እስካሁን አልተመረመረም። በአጠቃላይ አንድ አመት ያህል የዘለቀውን ግድያ የተባበሩት መንግስታት በገለልተኛ አካል እንዲመረመር የቀረበውን ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም። መንግስት ገለልተኛ አካል እንዳይገባ መከላከልና በሃገር ቤትም ገለልተኛ አካል እንዳይቋቋም ማድረጉ በአንድ አመት ውስጥ እጅግ የከፋ ዕልቂት ለመከሰቱ አመልካች እንደሆነም በፖለቲካ ተመልካቾች ዘንድ ታምኖበታል።