ጄ/ል ገብሬ አዲሱን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ነቀፉ

ሚያዝያ ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ራሳቸውን የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሕብረት -ኢጋድ የሶማሊያ ተወካይ አድርገው የሚቆጥሩት የቀድሞው በኢትዮጵያ የሶማሊያ ጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ገብሬ ዲላ ፣ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፎርማጆ በሶማሊያ ለተሰማሩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር አባላት አክብሮት አላሳዩም በሚል ነቅፈዋቸዋል።
ብ/ ጄኔራል ገብሬ በኦፊሻል የትዊተር ገጻቸው ላይ በጻፉት አጭር መልእክት ላይ እንዳሉት ”ፕሬዚዳንቱ በባይደዋ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ጦር አባላትን ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅት በተለይ ለኢትዮጵያ ጦር በዓደባባይ ንቀት አሳይተዋል ብለዋል”
የመጀመሪያውን ጽሁፍ ከለጠፉ ከሶስት ሰዓታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ፣ እኤአ በ 2010 ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ያደረጉላቸውን አቀባበልና ያደረጉትን ንግግር እንዴት ዘነጉት?” በማለት ቅሬታቸው ገልጸዋል።
በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ ባለስልጣናት መሃከል እየተካረረ የመጣውን አለመግባባት አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ከኢጋድም ሆነ ከአሚሶም በኩል ይፋዊ መግለጫ የሰጠ አካል የለም። አዲሱ የሲማሊያ ፕሬዚዳንት የኮምኒኬሽን ቢሮ በጉዳዩ ላይ ማስተባበያም ሆነ መግለጫ አልሰጠም።
በሶማሊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃላፊ የነበሩት ብ/ጄኔራል ገብሬ በእሁዱ የፕሬዚዳንት ፎርማጆ ጉብኝት ወቅት ባይደዋ ከተማ ውስጥ ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንቱ በባይደዋ ከተማ ጉብኝታቸው ወቅት በጸጥታ እና የድርቅ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል። ጄኔራሉ ከጉብኝቱ አስቀድሞ ከፕሬዚዳንት ሙሃመድ ጋር ለመገናኘት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ግን ሊቀበሉዋቸው አልፈለጉም።
የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ሰላም አስከባሪነት በብዛት መሰማራታቸውን እንደ ልዩ አጋጣሚ በመጠቀም ጄኔራሉ ጫና ለማሳደር ይሞክራል ሲሉ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ፕሬዚዳንት መሀመድ የሶማሊያን ሰላም እናመረጋጋት በዘላቂነት ለመፍታት ከሕዝባቸው ጋር ቀጥታ መወያየትን በመምረጥ ከኢትዮጵያ መንግስት የሚሰነዘርባቸውን ጣልቃገብነት እንዳማይቀበሉት ሶማሊያ አፕዴት ዘግቧል።
አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የደህንነት ሰራተኞቻቸውን የህወሃት/ኢህአዴግን ጣልቃ ገብነት በሚቃወሙ ጎሳ አባላት መሙላታቸው በኢህአዴግ በኩል ቅሬታ መፍጠሩን ኢሳት በማክሰኞ ምሽት ዘገባው ገልጾ ነበር። አብዛኞቹ የህወሃት የደህንነት አባላት ከሶማሊያ እንዲወጡ በመደረጋቸው ገዢው ፓርቲ፣ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ያገኝ የነበረው መረጃ እንዲቀንስበት አድርጓል። በአሁኑ ሰአት አብዛኛውነኢ መረጃ በአሚሶም በኩል እንደሚያገኝ የሚናገሩት ምንጮች፣ የአሚሶም መረጃዎች ጦራቸውን ወደ ሶማሊያ ላስገቡት አገራት እኩል የሚከፋፈል በመሆኑ፣ በሶማሊያ ውስጥ የነበረውን የመረጃ እና የሃይል የበላይነት እንዲያጣ ማድረጉን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና በማእከላዊ ሶማሊያ አልሸባብ በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ላይ የደፈጣ ጥቃት ፈጽሟል። በሂራን ግዛት ከባዳዋይኔ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በገጠሯ ቡርዳሌ አካባቢ ረቡዕ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ የአልሸባብ ሚሊሻዎች በኢትዮጵያ መከላከያ ኮንቮይ ተሽክርካሪ ላይ ባደረሱት ጥቃት አንድ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ማወደማቸውን እና ሁለት የኢትዮጵያ ወታደሮች መግደላቸውን በቃል አቀባያቸው በኩል መግለጫ ሰጥተዋል።
ሁለቱ ወገኖች መሃከላቸው ከፍተኛ ውጊያ አድርገዋል። አርቢጂን ጨምሮ በከባድ መሳሪያዎች ባደረጉት የተኩስ ልውውጡ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ስጋት እና ድንጋጤ ውስጥ መውደዋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
ከውጊያው በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሃይላቸውን በማጠናከር የቴሌኮምኒኬሽን መስመሮችን መበጣጠሳቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶም በበኩሉ ከባዳዋይኒ ከተማ ወደ ቡልቡርዴ ከተማ በመጉዋዝ ላይ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አምኗል። ከቅርብ ጊዜታ ወዲህ በሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ እና በሶማሊያ መንግስት ወታደሮች ላይ ተደጋጋሚ የደፈጣ ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል። አንዳንድ ከጠራማ አካባቢዎች በአልሸባብ ቁጥጥር ስር እየወደቁ ሲሆን በሂራን ግዛት ውስጥ ያሉ መስመሮችም ግኝኙነታቸው እየተቋረጠ መምጣቱንም ጋሮ ኦንላይን አክሎ ዘግቧል።