የሶማሊ ልዩ የሚሊሺያ አባላት የደሞዝ ጭማሪ ጠየቁ። ታጣቂዎቹ ትእዛዝ ለመቀበል ፈቀዳኛ አለመሆናቸውንም አስታውቀዋል

ሚያዝያ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ ከ200 ያላነሱ የኦሮሞ ተወላጆችን በመግደላቸው እየተወነጀሉ ያሉት በአቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር የሚመሩት የሶማሊ ልዩ ሚሊሺያ አባላት ፣የደረሰባቸውን ጥቃት ተከትሎ፣ የጉዳት ካሳና ደሞዝ ካልተጨመራቸው ማንኛውንም አይነት ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ለመዝመት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወደ አካባቢው በቅርቡ የተጓዙት አዲስ የተሾሙት የደህንነት አባል መከላከያው የልዩ ሃይሉን ቦታ ተክቶ የኦብነግን ጥቃት እንዲከላከል አዘዋል።
የሶማሊ ልዩ ሃይል አባላት ለደረሰባቸው ጉዳት ከጠየቁት የጉዳት ካሳ በተጨማሪ፣ 7 ሺ ብር ወርሃዊ ደሞዝ ካልተከፈላቸው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል። ሰራዊታቸው ለመታዘዝ ፈቃደኛ አለመሆኑን የተረዱት አቶ አብዲ፣ የግዛት ማስፋፋት እንቅስቃሴያቸውን ገትተው ከኦሮምያ አስተዳደር ጋር ድርድር ለማድረግና የሰላም ስምምነት በሚል ጊዜ መግዣ ስምምነት ለመፈራረም መገደዳቸውን የደህንነት ምንጮች ገልጸዋል። የልዩ ሚሊሺያ አባላት የጠየቁት ጥያቄ ተመልሶላቸው ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆኑ፣ አቶ አብዲ የጀመሩትን ጥቃት ሊቀጥሉ እንደሚችሉ እነዚህ ወገኖች ይናገራሉ።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው የተነሳውን የኮሌራ ወረርሽኝ በመፍራት እነሱም በኦብነግ ላይ ለመዝመት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ህወሃት ራሱ የሚተማመንባቸውን የሰራዊት አባላት በኦብነግ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ እንደላካቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለወራት የኢትዮጵያን የደህንነት አባላት ከአገሯ አስወጥታ የነበረችው ሶማሊላንድ ሰሞኑን ሁለት የደህንነት አባላት ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቅዳለች። ሶማሊላንድ በግዛቷ በተጠለሉ ኢትዮጵያውያን ላይ የህወሃት አገዛዝ ያለ ፈቃድ የሚወሰደውን እርምጃ እንዲሁም የመንግስቷን ተቃዋሚ መርዳቱ ያበሳጫት ሶማሊላንድ፣የደህንነት አባላቱ ከአገር እንዲወጡ ካዘዛች በሁዋላ፣ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን የጨመረ ድርድር በሁለቱ አገራት መካከል ሲካሄድ ቆይቷል።
ከአካባቢው ዜና ሳንወጣ በቅርቡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የደህንነት ሰራተኞች በአብዛኛው የህወሃት/ኢህአዴግን የሶማሊያ ወረራ ሲቃወሙ ከነበሩ ጎሳቸው የተውጣጡ መሆናቸው ገዢው ፓርቲን ያሳሳበ ጉዳይ ሆኗል።
የአለማቀፍ ደጋፍ እንደጠበቀው ባለማግኘቱ ሰራዊቱን ከሶማሊያ በማስወጣት ላይ ያለው የኢህአዴግ አገዛዝ፣ በሶማሊያ ያለው የደህንነት መዋቅሩ እየፈራረሰ መምጣቱን ሲያሳስበው የቆየ ቢሆንም፣ አሁን በአዲሱ የሶማሊ መንግስት ውስጥ የተካከቱ አብዛኞቹ የደህንነት አባላት፣ የእርሱን የሶማሊያ ፖሊሲ ከሚቃወሙ ጎሳዎች መመልመላቸው ይበልጥ ስጋት ላይ እንደጣለው ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።