በደቡብ ጎንደር ዞን ዜጎች በብዛት እየታሰሩ ነው

ሚያዝያ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት በቅርቡ ወዲህ በተለያዩ ሰበቦች በርካታ ዜጎች እየታፈሱ ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። የማሰር ዘመቻው ወደ ካህናቱም ወርዶ በትናንትናው እለት በአንዳቤት ወረዳ በርካታ ካህናት ቤተክርስቲያን ማስተዳደር አልቻላችሁም ተብለው ታስረዋል።
የደቡብ ጎንደር ሃገረ ሰብከት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት መላከ ሰላም አባ ሃይለየሱስ ቢያድግልኝ መታሰራቸውንም የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። የእርሳቸው መታሰር የአካባቢውን ህዝብ ከማስደንገጥ አልፎ አስቆጥቶታል።
“ ኢትዮጵያ ሌቦች እየተፈቱ መነኮሳት የሚታሰሩበት አገር ሆናለች” የሚሉት ነዋሪዎች፣ የአካባቢው ህዝብ የሚያደርገውን ተቃውሞ ለመስበር የተቃጣ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል በቃልቲ ዞን 1 ታስረው የሚገኙ የህሊና እስረኞች በእስር ቤት የሚደርስባቸውን በደል በመቃወም የረሃብ አድማ መጀመራቸው ታውቋል።
አድማው የተጀመረው ዛሬ ሲሆን፣ እስረኞቹ የሄደላቸውን ምግብ ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም።