ሚያዝያ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሕዝብ ቆጠራ ኮምሽን በመጪው ዓመት ህዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ አራተኛውን የህዝብና ቤት ቆጠራ እንደሚያካሂድ የኮምሽኑ ምንጮች ገለጹ።
የሕዝብና ቤት ቆጠራ በ10 ዓመት አንድ ጊዜ የሚከናወን ሲሆን ኮምሽኑ በ1999/2000 ዓ.ም ያካሄደው ሶስተኛው ቆጠራ የብአዴን/ኢህአዴግ የፓርላማ አባላትን ጭምሮ በርካታ ዜጎችን ያስቆጣ ነበር።
ኮምሽኑ ህዳር 25 ቀን 2001 ዓ.ም 3ኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ለፓርላማው ይፋ ሲያደርግ የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ ከትንበያው ዝቅ ብሎ ተገኝቶአል መባሉ ኮምሽኑ ተጨማሪ ፍተሻዎችን እንዲያደርግ አስገድዶታል።
ሆኖም ኮምሽኑ አካሂዶታል በተባለው ፍተሻ የቆጠራው አፈጻጸም ጭምር በዝርዝር ታይቶ የአማራ ክልል ሕዝብ ብዛት በተለየ መልኩ ሊያስቀንስ የሚችል ሁኔታዎች አለመኖራቸውን ተረጋግጦአል በሚል የቀረበውን ተቃውሞ አድበስብሶ አልፎታል።
በወቅቱ የፓርላማ አባላቱ ይፋዊ ጥያቄና ሙግት ያተኮረው የአማራ ክልል ሕዝብ ቁጥር ማነስ ቢሆንም ፣ የአዲስአበባ ሕዝብ ቁጥርም አንሶ መገኘቱ በብዙዎች ዘንድ ጉምጉምታንና የቆጠራውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ችትትን አስትሎ ነበር።
ቀደም ተብሎ የቀረቡት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች አስተማማኝ መልስ ባላገኙበት ሁኔታ በመጪው ህዳር ወር የሚካሄደው የህዝብ ቆጠራ ሌላ ውዝግብ ሊፈጥር እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።