ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የዓለማቀፉ ፕሬስ ኢንስቲትዩት የ2017 የፕሬስ ጀግኖች ሽልማት አሸናፊ ሆነ።

ሚያዝያ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዓለማቀፉ የፕሬስ ኢንስቲትዩት በምህጻረ ቃሉ- አይ ፒ አይ ይፋ እንዳደረገው፤69ኛውን የዓላማችን የፕሬስ ጀግኖች ሽልማት ፣ ፕሬስን ለማፈን የወጣውን የጸረ ሽብርተኝነት ህጉን በመተቸቱ ምክንያት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛና ጦማሪ እስክንድር ነጋ አሸንፏል። አይ ፒ አይ ዛሬ ባወጣው በዚሁ መግለጫ የአፍጋኒስታን ጋዜጠኞች ተከላካይ ኮሚቴ የነጻ ሚዲያ ሽልማት አሸናፊ መሆኑን አስታውቋል።
ሁለቱም ዓይነት ሽልማቶች ላለፉት ሦስት ዓመታት እየተሰጡ ያሉት መቀመጫውን ኮፐንሀገር ካደረገው ዓለማቀፉ የሚዲያ ድጋፍ አይ ኤም ኤስ ጋር በመተባበር ሲሆን፤ የሽልማት ሥነ ስርዓቱ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የፊታችን ግንቦት 18 የአይ ፒ አይ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በጀርመን ሀምቡርግ በሚካሄድበት ወቅት በሚሰናዳ ልዩ ፕሮግራም እንደሚሰጥ ተገልጿል። ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ድርጅት ራሳቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ጭምር ለፕሬስ ነጻነት በተለዬ መልኩ ታላቅ ድርሻ አበርክተዋል ያላቸውን ጋዜጠኞች የሚሸልምና የሚያከብር ድርጅት ነው።
እስክንድር ከመስከረም 2011 ወዲህ ከሁለት ሺህ በላይ ቀናትን በእስር ቤት ማሳለፉን ያወሳል አይ ፒ አይ ፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት-አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ለመክተት በማሴርና ከታገደ የተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው በማለት ክስ እንደመሰረቱበት ገልጿል።
እስክንድር ለእስር የተዳረገው የሽብርተኝነት ግሁ ጋዜጠኞችን ለመቅጣት የወጣ እንደሆነ በመጥቀስ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊንና አስተዳደራቸውን በተቸ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው።
ይህ የእስክንድር አስተያዬት ለማሰር ሰፊ ክፍተት ባለው በኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ አማካይነት፣ እስክንድርን የ2013 የዩኔስኮ ጉይሌርሞ ካኖ የዓለም ፕሬስ ነጻነት አሸናፊ ከሆኑት ከጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ከጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ እና ከስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ከማርቲን ሽብዬና ከዮኃን ፐርሶን ጋር ለእስር ዳርጎታል።
በ2012 የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ በመሳተፍና አመጽ ለመፍጠር በማቀድ፣በመዘጋጀትና በማሴር ክስ በእስክንድር ላይ የ18 ዓመት እስር መበየኑን የጠቀሰው የጋዜጠኞች መብት አስከባሪ ተቋሙ፤ ይህ ውሳኔ በመንግስታቱ ድርጅት ያለህግ በተፈጸሙ እስሮች ዙሪያ በሚሠራው ቡድን “ ዓለማቀፍ ህግጋትን የጣሰ”የሚል ውግዘት ማስከተሉን ገልጿል።
የአይ ፒ አይ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ባርባራ ትሪዮንፊ ፣ ሽልማቱ እስክንድር ነጋ ለሀሳብና ለመረጃ መንሸራሸር ላሳየው ድፍረት የተሞላበት ተግባር እንዲሁም በራሱ ነጻነት ላይና ከቤተሰቡ እስኪለይ ድረስ ፈርዶ ለፕሬስ ነጻነት ላሳዬው መሰጠት እውቅና የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት እስክንድር ነጋንና ሌሎች ሙያቸውን በመተግበራቸው ሳቢያ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች እንዲፈታ ጥሪያችንን ዳግም እናድሳለን” ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ዓለማቀፉ ማህበረሰብም ዓለማወፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጣስ እየቀጠለች ያለችውን ኢትዮጵያን በዝምታ እንዳይመለከት ግፊት እናደርጋለን ብለዋል።
ቀደም ካሉት ዓነታት ጀምሮ በተደጋጋሚ የታሰረውና እጆቹ እስኪሰባበሩ ድረስ ድብደባ የደረሰበት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከህጻን ልጁ ጋር በእግሩ በሚጓዝበት ጊዜ ከልጁ ፊት በደህንነቶች ታስሮ ወደ እስር ቤት ከተወረወረ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
እስክንድር ባለፉት ዓመታት ፔን ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ከአራት ድርጅቶች የፕሬስ ነጻነት ሽልማት አሸናፊ የሆነ ሲሆን፣ ምርጫ 97ትን ተከትሎ አብራው ታስራ የነበረችውና በወህኒ ቤት እንድትወልድ የተፈረደባት ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ደግሞ የዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ተንከባካቢ ድርጅት -ሲፒጄ እና የዓለማቀፉ ሴት ጋዜጠኞች ድርጅት ሽልማቶች አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል።