ሚያዝያ ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኘው ዶሎ ዞን በ30 አመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ምክያት በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ 16 ሺ ሰዎች መያዛቸውንና በየወሩም ከ3 ሺ 500 በላይ ሰዎች ወደ ህክምና ማእከል እንደሚገቡ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን አስታውቋል።
እንደ ድርጅቱ ዘገባ ከሆነ ወረርሽኙን ለመከላከል 1ሺ 200 ባለሞያዎች በ100 ጣቢያዎች አገልግሎት ለመስጠት ቢሞክሩም፣ ባካባቢው የመሰረተ ልማት አለመዘርጋት፣ የንጹህ ውሀ እጦት፣ የውሀ ማውጫ ፓምፖች ችግር እንዲሁም የትራንስፖርት እና መሰል ችግሮች ስራቸውን እንደወሳሰበባቸው አሳውቀዋል።
ድርጅቱ እርዳታ እያደረገ ባለበት አካባቢም ባለው የንጹህ ውሀ ችግር ህክምና ያደረገላቸው ተመልሰው ለወረርሽኙ እየተጋለጡ መምጣታቸውን ጠቁሞ ፣ አፋጣኝ እርዳታዎች የተጠየቁ ቢሆንም ከአለማቀፍ ድርጅቶች ምላሽ አለመገኘቱን ገልጿል።
በዚህ ከፍተኛ ድርቅና ወረርሽኝ ምክንያት ህብረተሰቡ የመኖርያ ቀየውን ለቆ እየተሰደደ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ በዋርዲስ ጤና ጣቢያ ከደረሱት መካከል አንድ እናት ስለሁኔታው ሲናገሩ ከብቶቻቸው በሙሉ በውሀ እጦት ማለቃቸውንና ልጃቸውም ከደረሰባት ወረርሽኝ በማገገም ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
አፋጣኝ የንጹህ ውሀ አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገ የብዙሀኑ የዶሎ ዞን ነዋሪዎች ህይወት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚወድቅና በሽታውም እንደገና ሊያገረሽ ይችላል በማለት ድርጅቱ አስጠንቅቋል።