ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2009)
በትምህርት ተቋማት የስነዜጋና የስነምግባር ግምባታና ዴሞክራሲያዊነት ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በሚል ርዕስ ሰሞኑን በተካሄደው መድረክ ላይ እንደተገለጸው በት/ቤቶች የሚሰጠው ይኸው የሲቪክ ትምህርት ውድቀት ገጥሞታል።
በአቶ አባይ ጸሃዬ የሚመራው የፖሊሲ ምርምር ማዕከል ባዘጋጀው በዚሁ መድረክ የአመራር ድክመት በዋና መንስዔነት ተቀምጦ ለአመታት ሲሰጥ የቆየው ትምህርት ውጤት አላመጣም ተብሏል። በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ አቋሞችን በሚያንጸባርቅ መልኩ ተዘጋጅቶ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጠው ትምህርት የተፈለገውን ውጤት ያላመጣው የፖለቲካ አመራር ላይ ባለው ድክመት መሆኑን አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ በረከት ስምዖን ተናግረዋል።
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በዋልታ ኢንፎርሜሽንና በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በጋራ ተደረገ የተባለውና የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ትምህርት ሚኒስቴርን ያላካተተው ጥናት ለስነ-ምግባርና ስነዜጋ ትምህርት መውደቅ ወይም ውጤት አለማምጣት የተለያዩ ምክንያቶች በዝርዝር ቢያስቀምጥም ዋናው ቁልፍ ችግር የፖለቲካው አመራር መዳከም እንደሆነ ተገልጿል። የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነጽሁፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል መምህርና ሃላፊ በዚሁ የስነምግባርና ስነዜጋ ትምህርት ቀረጻ ላይ የተሳተፉት ዶ/ር አብርሃም አለሙ እንደሚሉት ይህ የሲቪክ ትምርህት ቀድሞውኑ በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት የሚከተለውን የፖለቲካ ፕሮግራም ለማስረጽ ያቀደ እንጂ ጥሩ ምግባርና ሃገራዊ ፍቅር ያለው ትውልድ እንዲፈጠር የታለመ አልነበረም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በተሳተፉበትና የሲቪክ ትምህርት ውድቀት በተገለጸበት በዚሁ መድረክ በት/ሚኒስትሩ በዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያምና በሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት የመፍትሄ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን፣ በዋናነት የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ላይ ስርነቀል ለውጥ መምጣት እንዳለበት ተገልጿል።
ዶ/ር አብርሃም አለሙ በበኩላቸው የስነምግባርና የስነዜጋ ትምህርት መክሸፍ አጠቃላይ በስልጣን ላይ ያለውን ስርዓት ውድቀት ያሳያል ይላሉ።