ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። በክልሉ የእስረኛው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በመሄዱ የክልሉ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡበት ጠይቋል። እስረኞቹን ለማስተናገድ የተበጀተው በጀት ማለቁንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
እስረኞቹ በአማካኝ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በፍርድ ወይም ያለፍርድ በእስር እንደሚማቅቁ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ክልሉ ለ 22 ሺ 26 እስረኞች በቀን 9 ብር በድምሩ 203 ሺ 139 ብር፣ በአመት ደግሞ 73 ሚሊዮን 130 ሺ 40 ብር ወጪ ቢያደርግም፣ አሁን የእስረኞች ቁጥር በ3 እጥፍ በመጨመሩ ለማስተናገድ አለመቻሉን የክልሉ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የክልሉ ማረሚያ ቤት ለእስረኞች ህክምና ያወጣውን 2 ሚሊዮን 246 ሺ ብር ለመክፈል አልቻለም። የሁለት አመት ውዝፍ የህክምና ወጪ ለመክፈል ባለመቻሉም የጤና ተቋማት ለማስተናገድ ፈቃደኛ አንሆንም እያሉት መሆኑንም ገልጿል።
እያንዳንዱ እስረኛ በአማካኝ 5 ዓመት በእስር ቤት ቢቆይ በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 365 ሚሊዮን ፣ 200 ሺ ብር ምንም እሴት በማይጨምር ነገር ላይ ወጪ የደረጋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል።
የእስረኞች ቁጥር በአንዴ ያሻቀበው በ2008 ዓም የታየውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ የታሰሩ ወጣቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው።
ይህ አሃዝ በማረሚያ ቤት አስተዳደር ስር የሚገኙ እስረኞችን እንጅ በየወረዳው እና በየቀበሌው ታስረው የሚገኙትን ዜጎች ቁጥር አያካትትም። በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለአመት፣ ለወራት ወይም ለሳምንታት የሚታሰሩት እስረኞች ቁጥር ቢደመር በክልሉ የሚገኘው እስረኛ ቁጥር ከተጠቀሰው በብዙ እጅ ይልቃል።
በአማራ ክልል ያለውን የእስረኞች ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ህጋዊ በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደሚኖሩ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።