ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)
በሶማሌ ክልል በእርዳታ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለተለያዩ የሰብዓዊ ዕርዳታ ስራ የያዙትን በጀት እየተባባሰ ላለው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መከላከያ እንዲያዞሩ ተጠየቁ።
በሃገሪቱ መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት ዘንድ የሚካሄዱ የዕርዳታ ስራዎችን የሚያስተባብረው Ethiopian Humanitarian Fund በክልሉ በመዛመት ላይ ያለው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት ድርጅቶቹ በበጀታቸው ላይ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል። በሰባት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ በ40 ወረዳዎች ውስጥ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኮሌራ በሽታ ወረርሽኙ ለሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ከቀናት በፊት ቢያረጋግጥም የሟቾችን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
በክልሉ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለተወሰነ ጊዜ ትኩረታቸውን ሙሉ ለሙሉ የበሽታውን ወረርሽኝ መከላከል ላይ እንዲያተኩሩ ተጠይቀዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በበኩሉ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሲባል 68 ዶክተሮች 500 ነርሶችና በአጠቃላይ 1ሺ 200 የጤና ባለሙያዎች በአካባቢው እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የበሽታ ወረርሽኙ በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ ቢገልጽም፣ በበሽታው ምክንያት ምን ያክል ሰው እንደሞተ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
በሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ዕልባት ባለማግኘቱ ሳቢያ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኙ ሊቀሰቀስ መቻሉን የእርዳታ ድርጅቶችን ሲገልጽ ቆይተዋል።
ከዚሁ ከድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ ሰዎች በመሞት ላይ ቢሆኑም መንግስት መረጃን ይፋ ከማድረግ ተቆጥቧል።
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ተቀስቅሶ ከነበረው ተመሳሳይ የኮሌራ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ሰዎች ቢሞቱም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሟቾችን ቁጥር ይፋ ማድረጉ በታማሚዎች ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል በማለት መረጃውን እንዳልገለጸ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በመዛመት ላይ ያለው የኮሌራ በሽታ ወደ አጎራባች ክልሎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋትን ያሳደረ ሲሆን፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስጋቱን ግምት ውስጥ በመክተት በመዲናይቱ አዲስ አበባ ቅድመ መከላከል ስራ መጀመሩን አስታውቋል።
የውሃ አቅርቦት አለመኖር የበሽታውን ስርጭት ከሚያባብሱት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በኮሌራ በሽታ የተያዘ ሰው አፋጣኝ የህክምና ዕርዳታን ካላገኘ በቀናት ውስጥ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችልና በሽታው በፍጥነት የመዛመት ሁኔታ እንዳለውም ይነገራል።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸው ይታወቃል።
የመንግስት ባለስልጣናት የተረጂዎች ቁጥር በመጨመር ላይ መሆኑን በቅርቡ ቢያሳውቁም ቁጥሩ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የድርቅ አደጋ ካስከተለው የምግብ እጥረት በተጨማሪ ለተላለፊ በሽታዎች መቀስቀስ ምክንያት እንደሚሆን የተለያዩ አካላት ሲያሳስቡ ቆይተዋል።