አርሶአደሮች በደረሰኝ እየተጭበረበሩ ነው ተባለ

ሚያዝያ ፲ (አሥር) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢህአዴግ መንግስት የቁም ከብት በሚሸጡ አርሶአደሮች ላይ ያወጣው ተጨማሪ ክፍያ አርሶአደሮችን ለብዝበዛ እየዳረገ መሆኑን ገዳቱ የደረሰባቸው ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ በአንድ የቁም ከብት 3 ብር ይከፈልበት የነበረው ክፍያ ወደ 10 ብር ከፍ እንዲል መደረጉን አርሶአደሮች ቢቃወሙትም ሰሚ አላገኙም። ባለፈው ሳምንት በጉራጌ አካባቢ ገንዘቡን የሚሰበስቡ ሰዎች ከአርሶአደሮች በከብት 15 ብር እየተቀበሉ፣ ደረሰኙ ላይ ግን 3 ብር እየጻፉ ለአርሶአደሮች መስጠታቸውን የአይን እማኞች ተናግረው፣ ለምን ብለው የጠየቁ ሰዎች በፖሊሶች ማስፈራሪያ ተሰጥቷቸው ደረሰኙን እንዲቀዱ ተደርጓል።
በግልጽ ዝርፊያ እየተካሄደ ነው የሚሉት አርሶአደሮች፣ የመመሪያው አተገባበር የተዘበራረቀ በመሆኑ፣ ለብዝበዛ ተዳርገዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶአደሮች የተለመደውን 3 ብር ሲከፍሉ በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ 10 ብር ይከፍላሉ። በተለይ ማንበብ በማይችሉ በርካታ አርሶአደሮች ደረሰኝ ላይ ተጽፎ የሚታየው የገንዘብ መጠን አርሶአደሮች ከከፈሉት የተለየ መሆኑ በተደጋጋሚ ሪፖርት ቢደረገም፣ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ የሆነ አካል በመጥፋቱ አርሶአደሮች ብሶታቸው እንዲሰማላቸው ጠይቀዋል።