የዓለም የምግብ ድርጅት እና የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በኢትዮጵያ ለድርቅ ጉዳተኞች እርዳታ ለገሱ

ሚያዝያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሳኡዲ አረቢያ መንግስት እና የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) በጋራ ኢትዮጵያ ውስጥ አፋጣኝ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የርሃብ ተጠቂዎች የሚውል ረድኤት እርዳታ ለግሰዋል።
በደቡባዊ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል በድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ ርሃብ ተጋላጭ ለሆኑ የ127 ሽህ 666 ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል ለድንገተኛ አገልግሎት የሚውል እርዳታ ሰጥተዋል።
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በንጉስ ሳልማን የእርዳታ ማእከል አማካኝነት ዋጋቸው 1ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ 1 ሽህ 938 ቶን የምግብ እርዳታ አበርክተዋል። ለ103 ሽህ 040 ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን በምግብ ፓኬጅ በማቀፍ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ማቅረቡን የዓለም የምግብ ድርጅት (WFP) አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የዓለም የምግብ ድርጅት ዳሬክተር የሆኑት ጆን አይሊፍ እንዳሉት ”በኢትዮጵያ ለረሃብ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ወሳኙ ወቅት አሁን ነው። አሰቃቂ የሆነ የድርቅ አደጋ በአገሪቷ ላይ አንዣቧል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ይገኛል።” በማለት ተናግረዋል።
ጆን አይሊፍ አክለውም ”በሶማሌ ክልል ብቻ 1.7 ሚሊዮን ዜጎች አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በክልሉ በተፈጠረው የአየር መዛባት ምክንያት ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ነው። የአያሌ ዜጎች ሕይወት ከፍተኛ ተግዳሮት ውስጥ ወድቋል።” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በምስራቅ አፍሪካ በሕንድ ውቅያኖስ ሙቀት /Ocean Dipole/ ምክንያት የርሃብ አደጋው አዳምሱን እያሰፋ መምጣቱን እና በዚህ ዓመት ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ዥንዋ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ሳውድ አረቢያ ከ100 ሺ በላይ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ኢትዮጵያውያንን ከአገሯ ለማስወጣት ውሳኔ ማሳለፏ በአገሪቱ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ስጋት ፈጥሯል። ኢትዮጵያውያን በሚቀጥሉት ሶስት ወራት አገሪቱን ለቀው እንዲሄዱ የተጠየቁ ሲሆን፣ የሳውዲ መንግስት ትእዛዙን በማያከብሩት ላይ ከእስር ጀምሮ የተለያዩ ቅጣቶችን እንደሚጥል አስጠንቅቋል።