ሚያዝያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- እሁድ እለት ሕጋዊ የመግቢያ ሰነድ ሳይዙ ወደ ታንዛኒያ የገቡ 66 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መያዙን የታንዛኒያ የድንበር ፖሊስ አስታውቋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በተጨናነቀ ሁኔት ተጭነው ሲገቡ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዳሂር ኪዳቫሻሪ ተናግረዋል። ኮማንደር ዳሂር ”ኢትዮጵያዊያኑን ስደተኞች የጫነውን መኪና በፓትሮል ተከታትለን መንገድ በመዝጋት ኢሶንጄ ከተማ መቃረቢያ ላይ ይዘናቸዋል። ሁሉም ወንዶች ናቸው። ተጠርጣሪዎቹን በሙሉ ይዘን ለሚመለከተው የስደተኞች ጉዳይ አስረክበናቸዋል። ከታንዛኒያ ወደ ማላዊ ሕገወጥ ስደተኞችን የሚያዘዋውሩ ደላሎች አሉ። ይህን መስመር በመከታተል ምንጩን ማድረቅ እንፈልጋለን።” ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ስር ውለው በአስር ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንደሚከታተሉ ዘሲትዝን ዘግቧል።