ኢሳት (ሚያዚያ 9 ፥ 2009)
በቢሾፍቱ ከተማ የአህያ ስጋን እያዘጋጀ ለውጭ ሃገር ገበያ የሚያቀርበው ቄራ ከህዝቡ በተነሳ ተቃውሞና ጫና መዘጋቱ ተገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል የቢሾፍቱ አስተዳደርን ጠቅሶ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት የአህያ እርድ ቄራው መዘጋቱን አረጋግጧል።
የአህያ ስጋ ቄራው በመንግስት ፈቃድ ተሰጥቶት በቀን 2መቶ አህዮችን በማረድ ስጋውን እና ቆዳውን ወደ ቻይና መላክ ጀመሮ ነበር።
ጉዳዩ ከተሰማ በኋላ የአህያ ቄራው ከህዝቡ ሃይማኖት እና ባህል ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጉዳዩ ብዙዎችን አበሳጭቶና አሳዝኖ እንደነበር አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ኢንዶውመንት ባለስልጣን የአህያ ቄራ ፈቃድ ከ4 አመት በፊት ጀምሮ ለማንም እንዳይሰጥ ተወስኗል ቢልም ቀድመው ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ግን ስራው ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን አስታውቆ ነበር።
በዚህም መሰረት በቢሾፍቱ እና አሰላ የአህያ ቄራዎቹ ተከፍተው የአህያ ስጋ ቄራዎች ስራ እስኪጀምሩ ድረድ መንግስት ጉዳዩን በዝምታ ሲመለከት ቆይቷል።
ጉዳዩ በኢሳትና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ህዝብ ዘንድ ከደረሰ በኋላ ከፍተኛ ተቃውሞ በመቀስቀሱ የቢሾፍቱ አስተዳደር ከሚያዚያ 5፥ 2009 አም ጀምሮ የአህያ ቄራው እንዲዘጋ ወስኗል።
አስተዳደሩ ቆይቶም ቢሆን የአህያ ቄራን ከህዝቡ ሃይማኖትና ባህል ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንዲዘጋ ለመወሰን መገደዱን በመጨረሻ አስታውቋል።
ባለሃብቶቹ በሃገሪቱ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉ ስለሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ስራቸውን መቀጠል ይችላሉ መባሉንም ለማወቅ ተችሏል።
የአህያ ስጋ ቄራው እንዲሰራ የፈቀዱትም ሆነ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ስለመኖሩ ግን የተገለጸ ነገር የለም። የአህያ ቄራው ባለቤት የሆኑት ቻይናውያን ባለሃብቶች ኪሳራ አይጠይቁ ይጠይቁ የታወቀ ነገር የለም።