በደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አንድ ኢትዮጵያዊን ያቃጠሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 9 ፥ 2009)

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አንድ ኢትዮጵያዊ በገዛ ሱቁ ውስጥ በእሳት ተቃጥሎ ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን ሰኞ አስታወቀ።

አሰቃቂ የተባለው ይኸው የወንጀል ድርጊቱ በምስራቃዊ የኬፕ ግዛት ስር በምትገኘው የምስራቅ ለንደን ከተማ አቅራቢያ ቅዳሜ ምሽት ላይ መፈጸሙን የደቡብ አፍሪካ የማሰራጫ ኮርፖሬሽን (SABC) ዘግቧል።

ፖሊስ ድርጊቱ በምን ምክንያት ሊፈጸም እንደቻለ መረጃ አለመገኘቱን ገልጾ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በእሳት ቃጠሎው አደጋ ድንጋጤ እንደደሰባቸው አመልክቷል።

ስሙ ያልተገለጸው ኢትዮጵያዊ ከአንድ ወር በፊት የግል ሱቁን ከፍቶ እንደነበር የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የእሳት ቃጠሎው በደረሰ ጊዜ ከሱቅ ውስጥ ጩኸት ይሰማ እንደነበር እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ለ10 ደቂቃ ያህል ቆይቷል የተባለውን የኢትዮጵያዊውን ጩኸት ተከትሎ ነዋሪዎች ለእርዳታ ወደ ሱቅ ቢያመሩም ከአደጋው ሊያተርፉት አለመቻላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል።

በደቡብ አፍሪካ የሶማሌ ተወላጆች ማህበር አባል የሆነው አህመድ ሃሰን አሰቃቂው ድርጊቱ በውጭ ሃገር ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት ማሳደሩን ተናግረዋል።

የአካባቢው ፖሊስ የውጭ ሃገር ተወላጆች ችግር አጋጥሟቸው ለእርዳታ በሚሄዱ ጊዜ ምንም የሚሰጡት ድጋፍ የለም ሲል አህመድ ለቴለቪዥን ጣቢያው አስረድቷል። በሃገሪቱ የሚገኘው የሶማሌ ተወላጆች ማህበር በበኩሉ ድርጊቱን እንደሚያወግዝና ፖሊስ ተጠርጣሪን ይዞ ለፍትህ እንዲያቀርብ ጠይቋል።

የአስተዳደሩ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ሙላኪ ምቢ በበኩላቸው እስካሁን ድረስ ጥቃቱ በምን ምክንያት ሊደርስ እንደቻለ የታወቅ ነገር አለመኖሩን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ይሁንና ተጠርጣሪን ለመያዝ የአካባቢው ፖሊስ መጠነ ሰፊ ዘመቻን እያካሄደ እንደሆነ ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የውጭ ሃገር ዜጎች ላይ ሲፈጸም የቆየውን ጥቃት ተከትሎ በኢትዮጵያዊው ላይ የደረሰውን ጥቃት የመጀመሪያው መሆኑ ታውቋል።

በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሃገሬው ተወላጆች የሚፈጸመውን የጥላቻ ጥቃት ማስቆም አልቻለም ሲሉ ተቃውሞን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የአፍሪካ ህበረት በበኩሉ የፕሬዚደንት ጃኮብ ዙማ መንግስት ለውጭ ሃገር ተወላጆች አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ በወቅቱ አሳስቧል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ በግልና በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ዝፊያን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች እንደሚፈጸምባቸው መረጃዎች ያመለክታል።