ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ኦጋዴን አካባቢ በምትገኘው የብርቆድ ከተማ በመዛመት ላይ ባለ የኮሌራ በሽታ ወረርሽን 50 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
በአካባቢው በመንግስት የተጣለው የንግድና የሰዎች ዝውውር እገዳ የበሽታው ስርጭት ወደ ከፋ ደረጅ እንዲሸጋገር ማድረጉን መቀመጫውን በቤልጅየም ብራሰልስ ከተማ ያደረገውና Unrepresented Nations and People’s Organization (UNDO) የተሰኘው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅት የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።
በዚሁ የኮሌራ በሽታ ወረርሽን በሚያዚያ ወር ብቻ ቆርሌ ተብሎ በሚጠራ መንደር 44 ሰዎች መሞታቸውንና በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ለህመም እንዲሁም ለምግብ እጥረት ተጋልጠው እንደሚገኙ ተመልክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ ለኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት መሆኑንና ሰዎች መሞት መጀመራቸውን ከቀናት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የዚሁ መረጃ መሰራጨት ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ ተመሳሳይ ሪፖርትን ያወጣው የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ እያደረሰ ያለውን የሰዎች ሞት እንዳይታወቅ ነዋሪዎችን ከቀያቸው በማፈናቀል የሞቱ ሰዎችን በድብቅ እንደቀበረ መሆኑን አመልክቷል።
የክልሉና የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ድርቁ በአካባቢው አስከፊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ቢገልፅም በሰው ላይ ስለደረሰ ጉዳት የሰጡት መረጃ የለም።
ቆርሌ ተብሎ በሚጠራ የዶሎ ወረዳ ከተማ በየዕለቱ የሚሞቱ ሰዎች በመኖራቸው የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የሰብዓዊው መብት ተሟጋች ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
ይኸው ድርጅት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ በቅርቡ ሰፊ ሪፖርትን ያወጣ ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቂ ትኩረት አልሰጠም ሲል ቅሬታ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።
በዚሁ የሶማሌ ክልል የድርቅ አደጋ ዙሪያ ዘገባን ያቀረበው የኦጋዴን ዜና (ኤጀንሲ) አውታር በበኩሉ በደገሃቡር እና ዙሪያዋ ባሉ የገጠር መንደሮች ህጻናትን ጨምሮ ነዋሪዎች በኮሌራ በሽታ ወረርሽኝና በምግብ እጥረት ህይወታቸው እያለፈ መሆኑን የሟቾችን ስም በመዘርዘር ዘግቧል።
በኦጋዴን አካባቢ ተጥሎ ያለው የንግድና የሰዎች ዝውውር በአስቸኳይ እንዲነሳ ነዋሪዎች ጥያቄ ማቅረባቸውም ታውቋል።
መንግስት በዚሁ አካባቢ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የሚያደርገውን ጥቃት ለመመከት በሚል ከጥቂት አመታት በፊት ወታደሮችን በማሰማራት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም ጋዜጠኞች ወደ ስፍራው እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው።
በዚሁ እገዳ ምክንያት በክልሉ ጉዳት እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋና የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እያገኘ አለመሆኑን የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል በመዛመት ላይ ባለው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ሰዎች በመሞት ላይ መሆናቸውን ቢያረጋግጥም የሟቾችን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ስድስት ዞኖች ውስጥ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በሰው ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አርብ አረጋግጧል።