በአዲስ አበባ ፍተሻው ተጠናክሮ ቀጥሎአል

ሚያዝያ ፭ (አምስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ወኪላችን እንደዘገበው ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በፒያሳ አካባቢ የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት የሚታዩ ሲሆን ፣ ምሽት ላይ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በሚያመሩበት ጊዜ ፍተሻ ያደርጋሉ።
አንዳንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ነዋሪዎችን በሚፈትሹበት ወቅት ‘ አይዟችሁ አትፍሩ ታዘን ነው የምንፈትሸው እንደሚሉ” ወኪላችን ገልጿል። የገዢው ፐርቲ የደህንነት አባላት በአሉን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ብዙዎቹ ስጋት አለባቸው ወደሚባሉ ቀጠናዎች ለመረጃ ማሰባሰብና ለስለላ ስራ ተሰማርተዋል።
የደህንነት አባላቱ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ ክልሎች ያመሩ ሲሆን፣ በበአል ወቅት ወደ ትውልድ ቀያቸው የሚያመሩትን ወጣቶች የሲቪል ልብስ ለብሰው እንዲሰልሉ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል።
ገዢው ፓርቲ ልዩ ትኩረት በሚያደርግባቸው የአማራ እና ኦሮምያ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ለበአሉ በሚሰባሰቡበት ወቅት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚመክሩት ምንጮቻችን፣ በተለይ ከማያውቁዋቸው ሰዎች ጋር የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ወይም የፖለቲካ አመለካከትን ማጋራት አደገኛ ነው ይላሉ።