ሚያዝያ ፭ (አምስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ተቋም ከመጋቢት እስከ ግንቦት ወራት ድረስ የሚጥለው የዝናብ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ20 እስከ 30 ቀናት ዘግይቶ እንደሚጀምር እና የዝናቡም መጠን በአማካኝ ከነበረው አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል በወርሃዊ ሪፖርቱ ገልጿል። በድርቅ ክፉኛ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የዝናብ ስርጭቱ ከ30 እስከ 40 ቀናት ዘግይቶ ይጥላል የሚል ስጋት በመኖሩ፣ የርሃቡ አደጋ በሶማሊያ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ነዋሪ የሆኑ አርብቶ አደሮች ሕይወት ላይ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ሲል ተመድ አስጠንቅቋል።
ድርቁ ባስከተለው ችግር ምክንያት አያሌ ዜጎች በርሃብ እና በኮሌራ ወረሽኝ ሕይወታቸውን እያጡ ሲሆን ከ4 ሺ በላይ የኮሌራ ወረሽኝ ተጠቂ ሕጻናቶች በሶማሊያ ክልል መኖራቸውን ሪፖርት መደረጉንም የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) አስታውቋል። ከሶማሊያ ክልል በተጨማሪም በደቡብ ክልል እና በኦሮሚያም የምግብ እጠረት እና ተላላፊ በሽታዎች እየተዛመቱ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል። በተላላፊ የኮሌራ በሽታ የሕጻናት ሕይወት ከመጥፋቱ አስቀድሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ለረድ ኤት ድርጅቶች ተማጽኖ አቅርቧል።
አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ ”በኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ እና ርሃብ እንዳይከሰት የማድረግ አቅም አለን። ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ናይጀሪያን፣ የመንን እና ሶሪያን እንጂ ኢትዮጵያ ድጋፍ አያስፈልጋትም” ብለው ነበር።
የእንግሊዝ ዓለምአቀፍ እድገት ሚንስትር የሆኑት ጀምስ ዋርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት 4.2 ሚሊዮን የሚሆኑ በረሃብ የተጠቁ ዜጎችን ሕይወት መንግስታቸው መታደጉን ተናግረዋል። የእንግሊዝ መንግስት 2.5 ሚሊዮን ሕጻናት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲከታተሉ ለማስቻል፣ 4.9 ሚሊዮን የንጹህ ውሃ እና የንጽህና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም ግማሽ ሚሊዮን እናቶች ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ጀምስ ዋርሰን እንደሚሉት እንግሊዝ 13 ሚሊዮን የርሃብ ተጠቂ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ነድፋ ድጋፍ እያደረገች ሲሆን ፣ መንግስታቸው በድርቁ የተጠቁ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ለመታደግ የሚውል የ11.5 ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ እርዳታ መስጠቱን ገልጸዋል።
የኳታር መንግስት በበኩሉ በርሃብ ለተጎዱ ኢትዮጵያዊያን የሚውል 5 ሚሊዮን ድርሃም እና የቁሳቁስ እርዳታ በሸህ ታአኒ ቢን አብዱላህ ፋውንዴሽን አማካኝነት መለገሱ ታውቋል። የኢትዮጵያዊ መንግስት ባቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ጥሪ መሰረት እርዳታ መስጠቱን የገለጸው የካታር መንግስት፣ ተጨማሪ ሰብዓዊ እርዳታዎችን እንደሚያደርግ መግለጹን ገልፍ ታይምስ ዘግቧል።
በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው የሰብል ትል በድርቅ በተጠቃው አርሶአደር ላይ ተጨማሪ አደጋ ይዞ መምጣቱ ታውቋል። ሰብል አውዳሚ ትሎች በአካባቢው እየተስፋፋ ከመጣው ድርቅ እና ርሃብ ጋር ተዳምሮ በዜጎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መምጣቱን የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሚንስቴር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልል በ10 ሽህ 700 ሄክታር ላይ የሚገኙ ማሳዎች በተዛማጅ የሰብል ትሎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።