ሚያዝያ ፭ (አምስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእየለቱ ብዙ የሚባልለት የኢትዮጵያ ባለሁለት አሃዝ ኢኮኖሚ እድገት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምን እጅግም አልመሰጠው። ዘንድሮም ድርጅቱ አገሪቱን በአለም እጅግ ድሃ ከሚባሉ አገራት ተራ መድቧታል። ምንም እንኳ ባለፉት 25 ዓመታት መሻሻሎች ቢኖሩም ፣ ኢትዮጵያ በብዙ መስፈርቶች አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ሰብአዊ ልማት ( Low Human Development Category) ካላቸው አገራት ተርታ ትመደባለች ያለው የልማት ፕሮግራሙ፣ ጥናቱ ከተካሄደባቸው 188 አገራት 174ኛ ላይ አስቀምጧታል።
የተመድ የልማት ፕሮግራም ጥናት የኢኮኖሚ እድገትን፣ የሃብት ክፍፍልን፣የስራ እድል፣ የትምህርት፣ የጤና፣ ሰላም፣ ፍትህ፣ ነጻነት እና የጾታ እኩልነትን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚታሰብ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአብዛኛው መስፈርቶች ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር እንኳን ስነጻጸር ዝቅተኛ ውጤት ተሰጥቷታል።
አብዛኛውን ንጽጽር ጎረቤት አገራት ከሆኑት ሩዋንዳና ዩጋንዳ ጋር በማድረግ ጥናቱን የሰራው ድርጅቱ፣ ሩዋንዳና ዩጋንዳ በብዙ መስፈርቶች ከኢትዮጵያ ተሽለው በመገኘታቸው የ159ነኛ እና የ160ኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል። ከሰሃራ በታች ያሉ አገራትን የሰብአዊ ልማት ለመመዘን የተቀመጠው መስፈርት 0.523 ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ያገኘችው ነጥብ ከዚህም አንሶ 0.448 መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል። በኢትዮጵያ ተመዘገበ የሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ብዙሃኑን የረሳና ጥቂቶችን ብቻ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል።
ከኢትዮጵያ በታች የኢኮኖሚ እድገት ያገኙት በሙሉ የአፍሪካ አገራት ናቸው።በሰው ልማት ሃብቷ ኖርወይ በአንደኝነት ስትቀመጥ፣ አውስትራሊያ፣ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ሲንጋፖር፣ ኔዘርላንድስ፣ አይርላንድ፣ አይስላንድ ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ይከተላሉ።
የኢህአዴግ አገዛዝ ባለፉት 10 ዓመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንዳገኘ በየቀኑ ቢናገርም፣ የኢትዮጵያ የስብአዊ ልማት ደረጃ ካለበት ደረጃ ፈቀቅ አላለም። የተመድ የልማት ፕሮግራም፣ አገሪቱ በበርካታ ጉዳዮች ስራ መስራት እንዳለበት ምክሩን አሳርፏል።