በይርጋለም የታሰሩት የመንግስት ሰራተኞች በእስር እንዲቆዩ ውሳኔ ተላለፈባቸው

ሚያዝያ ፭ (አምስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ በአንድ ጊዜ ከ10 በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ የሲዳማ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰራተኞች ያቀረቡትን የዋስ መብት ጥያቄ ባለመቀበል ለተጨማሪ 10 ቀናት በእስር ቤት እንዲቆዩ ወስኗል።
በግለሰቦቹ ላይ የቀረበው ክስ የበሉትን አበል አላወራረዱም የሚል መሆኑን ችሎቱን የተከታተሉ ሰዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ምንጮች እንደሚሉት ግን በጅምላ የተደረገው እስር ጥልቅ ተሃድሶ በሚል ግምገማ ከተካሄደ በሁዋላ ሲሆን፣ በሙስና የተዘፈቁ ዋና ዋና አመራሮችን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመመደብ፣ ተራ ሰራተኞችን በማሰር ህዝቡን ለመሸንገል የተወሰደ እርምጃ ነው። የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች እንታሰር ይሆናል በሚል ከአካባቢው መልቀቃቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።